ይሁዳም ወደ ዮሴፍ ቀረብ ብሎ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ አንዲት ቃል ብቻ ልናገር፤ አንተም የፈርዖንን ያህል የተከበርህ ስለ ሆንህ፣ እባክህን እኔን አገልጋይህን አትቈጣኝ። ጌታዬ፣ ‘አባት ወይም ወንድም አላችሁ?’ ብሎ አገልጋዮቹን ጠይቆ ነበር። እኛም፣ ‘አዎን፣ ሽማግሌ አባት አለን፤ አባታችንም በስተርጅና የወለደው ትንሽ ልጅ አለው፤ ወንድምየው ሞቷል፤ ከአንድ እናት ከተወለዱት ልጆች መካከል የተረፈው እርሱ ብቻ ነው፤ አባቱም በጣም ይወድደዋል’ ብለንህ ነበር። “ከዚያም አንተ አገልጋዮችህን፣ ‘እንዳየው ወደ እኔ አምጡት’ አልኸን። እኛም ለጌታዬ ‘ልጁ ከአባቱ ሊለይ አይችልም፤ ከተለየው ደግሞ አባትየው ይሞታል’ አልንህ። አንተ ግን እኛን አገልጋዮችህን፣ ‘ታናሽ ወንድማችሁ ዐብሯችሁ ወደዚህ ካልመጣ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ አልኸን። እኛም ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ በተመለስን ጊዜ፣ አንተ ጌታዬ ያልኸንን ነገር ነው። “ከዚያም አባታችን ‘እስኪ ተመልሳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን’ ሲለን፤ ‘መሄድ አንችልም፤ መሄድ የምንችለው ታናሽ ወንድማችን ዐብሮን ሲሄድ ብቻ ነው። ታናሽ ወንድማችንን ይዘን ካልሄድን በቀር፣ የሰውየውን ፊት ማየት አንችልም’ አልነው። “አገልጋይህ አባቴም እንዲህ አለን፤ ‘ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆች እንደ ወለደችልኝ ታውቃላችሁ፤ አንዱ በወጣበት በመቅረቱ፣ “በርግጥ የአውሬ እራት ሆኗል” አልሁ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይኸው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። አሁን ደግሞ ይህን ልጅ ወስዳችሁ አንዳች ጕዳት ቢደርስበት ሽበቴን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።’ “እንግዲህ አሁን ልጁን ሳንይዝ ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ ብመለስ፣ ሕይወቱ ከልጁ ሕይወት ጋራ በጥብቅ የተሳሰረ ስለ ሆነ፣ የልጁን ከእኛ ጋራ አለመኖር ሲያይ አባቴ ይሞታል። ከዚህም የተነሣ እኛ አገልጋዮችህ የአባታችንን ሽበት በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር እናወርደዋለን። እኔ አገልጋይህ፣ ‘ልጅህን መልሼ ሳላመጣ ብቀር፣ ለዘላለም በደለኛ አድርገህ ቍጠረኝ’ በማለት፣ ስለ ልጁ ደኅንነት በአባቴ ፊት ራሴን ዋስ አድርጌአለሁ። “ስለዚህ አሁን፣ አገልጋይህ በልጁ ፈንታ የአንተ የጌታዬ ባሪያ ሆኜ እዚሁ ልቅር፤ ልጁ ግን ከወንድሞቹ ጋራ ይመለስ። ልጁን ሳልይዝ እንዴት ተመልሼ ወደ አባቴ እሄዳለሁ? ፈጽሞ አላደርገውም፤ እባክህ በአባቴ ላይ የሚደርሰውን መከራ እንዳይ አታድርገኝ።”
ዘፍጥረት 44 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 44
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 44:18-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos