የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 40

40
ዮሴፍ የእስረኞቹን ሕልም መተርጐሙ
1ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን የወይን ጠጅ አሳላፊና የእንጀራ ቤት ኀላፊ ንጉሡን የሚያሳዝን በደል ፈጸሙ። 2ፈርዖን በወይን ጠጅ አሳላፊውና በእንጀራ ቤት ኀላፊው እጅግ ተቈጣ። 3ስለዚህ ዮሴፍ ታስሮ ወደሚገኝበት ወደ ዘበኞች አለቃ ቤት ተወስደው እንዲታሰሩ አደረገ። 4የእስር ቤቱም አዛዥ ለዮሴፍ አስረከባቸው፤ ዮሴፍም ያገለግላቸው ነበር። በእስር ቤትም ለጥቂት ጊዜ ቈዩ።
5የንጉሡ የወይን ጠጅ አሳላፊና የእንጀራ ቤት ኀላፊ ሁለቱም በእስር ቤት ሳሉ በአንድ ሌሊት ሕልም አዩ፤ የእያንዳንዳቸው ሕልም የተለያየ ትርጒም ነበረው።
6በማግስቱ ጠዋት ዮሴፍ እነርሱ ወዳሉበት ክፍል በገባ ጊዜ ተክዘው አገኛቸውና፥ 7“ዛሬ በፊታችሁ ላይ ሐዘን የሚታየው ለምንድን ነው?” አላቸው።
8እነርሱም “እያንዳንዳችን ሕልም አየን፤ ነገር ግን የእያንዳንዳችንን ሕልም የሚተረጒም ማንም የለም” አሉት።
ዮሴፍም “ሕልም የመተርጐም ችሎታ የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ የእያንዳንዳችሁን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው።
9የወይን ጠጅ አሳላፊው እንዲህ በማለት ሕልሙን ተናገረ፤ “በሕልሜ አንድ የወይን ተክል አየሁ፤ 10በተክሉም ላይ ሦስት ሐረጎች ነበሩ፤ ቅጠሉ ለምልሞ ወዲያው አበባ አወጣ፤ የወይን ዘለላውም ወዲያው በሰለ፤ 11የፈርዖን ጽዋ በእጄ ነበረ፤ የወይኑን ፍሬ ወስጄ በጽዋው ውስጥ ጨመኩና ጽዋውን ለፈርዖን ሰጠሁት።”
12ዮሴፍም እንዲህ አለ፤ “የሕልሙ ትርጕም ይህ ነው፤ ሦስቱ የወይን ሐረጎች ሦስት ቀኖች ናቸው፤ 13በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ ንጉሡ ከእስራት ይፈታሃል፤ በደልህንም ይቅር ብሎ ወደ ቀድሞው ማዕርግህ ይመልስሃል፤ ቀድሞ የመጠጥ ቤት ኀላፊ ሆነህ ታደርገው እንደ ነበር የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጠዋለህ። 14ነገር ግን ሁሉ ነገር በተቃናልህ ጊዜ እኔን አስታውሰህ እርዳኝ፤ ለፈርዖንም አሳስበህ ከእዚህ ከእስር ቤት እንድወጣ አድርገኝ። 15እኔ ከዕብራውያን አገር ወደዚህ የመጣሁት ወድጄ ሳይሆን ተሸጬ ነው፤ እዚህም አገር ከመጣሁ ወዲህ በእስር ቤት የምገኘው ምንም በደል ሳልፈጽም ነው።”
16የእንጀራ ቤት ኀላፊውም ዮሴፍ ለወይን ጠጅ አሳላፊው ሕልም የሰጠው ትርጒም መልካም መሆኑን ባየ ጊዜ፥ የእርሱንም ሕልም ለዮሴፍ እንዲህ ብሎ ነገረው፤ “እኔም በበኩሌ ያየሁት ሕልም ይህ ነው፤ ‘ሦስት መሶብ እንጀራ በራሴ ላይ ተሸክሜ ነበር፤ 17ከሁሉ በላይ ባለው መሶብ ውስጥ ለፈርዖን የተዘጋጀ ልዩ ልዩ ምግብ ነበረበት፤ ነገር ግን ወፎች ምግቡን ከመሶቡ እያነሡ ይበሉት ነበር።’ ”
18ዮሴፍም “የሕልሙ ትርጒም እንዲህ ነው፤ ሦስት መሶቦች ሦስት ቀኖች ናቸው፤ 19በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ ፈርዖን ከዚህ እስር ቤት አውጥቶ ራስህን ካስቈረጠ በኋላ በእንጨት ላይ ያሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።”
20በሦስተኛው ቀን የፈርዖን ልደት በዓል ስለ ነበረ ለመኳንንቱ ሁሉ ግብዣ አደረገ፤ በዚያኑ ቀን የወይን ጠጅ አሳላፊውና የእንጀራ ቤት ኀላፊው ከእስር ቤት ወጥተው በመኳንንቱ ፊት እንዲቀርቡ አደረገ። 21የወይን ጠጅ አሳላፊውን ወደ ቀድሞ ማዕርጉ መለሰው፤ ስለዚህ የወይን ጠጅ ጽዋውን ለንጉሡ መስጠት ጀመረ። 22የእንጀራ ቤት ኀላፊውን ግን እንዲሰቀል አደረገው፤ ሁሉም ነገር ዮሴፍ የእያንዳንዳቸውን ሕልም እንደ ተረጐመው ሆነ።
23የወይን ጠጅ አሳላፊው ግን ዮሴፍን አላስታወሰውም፤ ስለ ዮሴፍ የሆነውን ሁሉ ረሳ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ