የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 34

34
የያዕቆብ ሴት ልጅ የዲና መደፈር
1ከዕለታት አንድ ቀን ልያ ለያዕቆብ የወለደችለት ዲና በዚያ አካባቢ የሚኖሩትን ከነዓናውያት ሴቶች ለማየት ወጣች፤ 2የአገሩ ገዢ የሒዋዊው የሐሞር ልጅ ሴኬም ባያት ጊዜ ያዛት፤ በማስገደድም ክብረ ንጽሕናዋን ደፈረ። 3በውበቷ ተማርኮ እጅግ ወደዳት፤ እርስዋም እንድትወደው ለማድረግ በፍቅር ቃል አነጋገራት። 4አባቱንም “ከዚህች ልጅ ጋር አጋባኝ” አለው።
5ያዕቆብ ልጁ ዲና ክብረ ንጽሕናዋ እንደ ተደፈረ ሰማ፤ ነገር ግን ወንዶች ልጆቹ የከብት መንጋ ይዘው ተሰማርተው ስለ ነበር፥ እነርሱ እስከሚመጡ ዝም ብሎ ቈየ፤ 6ከዚህ በኋላ የሴኬም አባት ሐሞር፥ ያዕቆብን ለማነጋገር ወጣ፤ 7ልክ በዚያኑ ጊዜ የያዕቆብ ልጆች ከተሰማሩበት መጡ፤ ስለ ተፈጸመው ድርጊት በሰሙ ጊዜ እጅግ ደነገጡ፤ ይህ ነገር መደረግ ስላልነበረበት ሴኬም የያዕቆብን ልጅ በመድፈር የእስራኤልን ሕዝብ በማዋረዱም እጅግ ተቈጡ። 8ሐሞር ግን እንዲህ አላቸው፤ “ልጄ ሴኬም ልጃችሁን በጣም ወዶአታል፤ ስለዚህ እንዲያገባት ፍቀዱለት፤ 9እንዲያውም በመካከላችን የጋብቻ ውል እናድርግ፤ እኛ የእናንተን ሴቶች ልጆች እናግባ፤ እናንተም የእኛን ሴቶች ልጆች አግቡ። 10በዚህ ዐይነት በአገራችን ላይ ከእኛ ጋር መኖር ትችላላችሁ፤ በፈለጋችሁበት ስፍራ በመዘዋወር እየሠራችሁና እየነገዳችሁ ርስትም ይዛችሁ መኖር ትችላላችሁ።”
11ሴኬምም፥ በበኩሉ የዲናን አባትና ወንድሞችዋን እንዲህ አላቸው፤ “ሐሳቤን ብትፈጽሙልኝ የምትፈልጉትን ሁሉ አደርጋለሁ፤ 12ለሙሽራዋም ጥሎሽ የፈለጋችሁትን ያኽል ጠይቁኝ፤ እርስዋን እንዳገባ ፍቀዱልኝ እንጂ፥ የፈለጋችሁትን ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ።”
13ሴኬም እኅታቸውን ዲናን አስነውሮ ስለ ነበር የያዕቆብ ልጆች ለእርሱና ለአባቱ ለሐሞር በተንኰል እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ 14“እኅታችንን ያልተገረዘ ሰው እንዲያገባት አንፈቅድም፤ ይህ ለእኛ ታላቅ ውርደት ነው፤ 15እርስዋን ለመስጠት የሚያስችለን አንድ መንገድ ብቻ አለ፤ ይኸውም አንተና የአገርህ ወንዶች ሁሉ እንደኛ የተገረዛችሁ እንደ ሆነ ነው። 16እንዲህ ከሆነ እናንተ የእኛን ሴቶች ልጆች ታገባላችሁ፤ እኛም የእናንተን ሴቶች ልጆች እናገባለን፤ አንድ ሕዝብ ሆነንም አብረን እንኖራለን። 17ሐሳባችንን ባትቀበሉና ባትገረዙ ግን እኅታችንን ይዘን እንሄዳለን።”
18ይህም አባባል ለሐሞርና ለልጁ ለሴኬም መልካም መስሎ ታያቸው፤ 19ሴኬም፥ የያዕቆብን ልጅ እጅግ ወዶአት ስለ ነበር የተነገረውን ሁሉ ለማድረግ ምንም ጊዜ አልወሰደበትም፤ ከዚህም በላይ በቤተሰቡ ውስጥ እጅግ የተከበረ በመሆኑ የፈለገውን ለማድረግ መብት ነበረው።
20ስለዚህ ሐሞርና ልጁ ሴኬም በከተማው በር አጠገብ ወዳለው መሰብሰቢያ ቦታ ሄዱ፤ ለከተማይቱ ነዋሪዎች እንዲህ በማለት ንግግር አደረጉ፤ 21“እነዚህ ሰዎች ከእኛ ጋር የሚኖሩት በሰላም ነው፤ በምድሪቱ ላይ አብረውን ይቀመጡ፤ በነጻም ይዘዋወሩባት፤ እነሆ፥ ምድሪቱ ለእኛም ለእነርሱም ትበቃናለች፤ የእነርሱን ሴቶች ልጆች እናግባ፤ የእኛንም ሴቶች ልጆች እንዳርላቸው። 22ሆኖም እነዚህ ሰዎች አብረውን ለመኖርና ከእኛም ጋር አንድ ሕዝብ ለመሆን ፈቃደኞች የሚሆኑት ወንዶች የሆንን ሁሉ እንደ እነርሱ ለመገረዝ የተስማማን እንደ ሆነ ነው። 23እንዲህ ብናደርግ መንጋዎቻቸውና ከብቶቻቸው፥ ሌላውም ንብረታቸው ሁሉ የእኛ ይሆን የለምን? ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ስምምነት እናድርግ፤ እነርሱም ከእኛ ጋር ይኑሩ።” 24የከተማይቱ ነዋሪዎች ሁሉ ሐሞርና ሴኬም ባቀረቡት ሐሳብ ተስማምተው ወንዶች ሁሉ ተገረዙ።
የዲና ወንድሞች በቀል
25በሦስተኛው ቀን ሰዎቹ ገና ከመገረዝ ቊስል ሳይድኑ ከያዕቆብ ልጆች መካከል ሁለቱ የዲና ወንድሞች ስምዖንና ሌዊ ሰይፍ፥ ሰይፋቸውን ይዘው ማንም ሳያውቅባቸው፥ ወደ ከተማ ገቡና ወንዶቹን ሁሉ ገደሉ። 26ሐሞርንና ልጁን ሴኬምን ሳይቀር በሰይፍ ከገደሉ በኋላ፥ ዲናን ከሴኬም ቤት ወስደው ሄዱ። 27የቀሩትም የያዕቆብ ልጆች ወደሞቱት ሰዎች ቤት እየገቡ እኅታቸው የተደፈረችበትን ከተማ በሙሉ ዘረፉ። 28የበግና የፍየል መንጋዎቻቸውን፥ ከብቶቻቸውን፥ አህዮቻቸውንና በከተማና ከከተማ ውጪ የነበራቸውን ንብረት ሁሉ ዘርፈው ወሰዱ። 29ሴቶችንና ሕፃናትን ማረኩ፤ በየቤቱ ያገኙትን ሀብት ሁሉ ዘረፉ።
30ያዕቆብ ስምዖንንና ሌዊን እንዲህ አላቸው፤ “በእኔ ላይ ከባድ ችግር አመጣችሁብኝ፤ እነሆ በዚህ ድርጊት የተነሣ በዚህች ምድር የሚኖሩ ከነዓናውያንና ፈሪዛውያን ይጠሉኛል፤ እኛ በቊጥር አነስተኞች ነን፤ እነርሱ ተባብረው ቢያጠቁን እኔና ቤተሰቤ እንጠፋለን።”
31እነርሱ ግን “እኅታችን እንደ አመንዝራ ሴት ትደፈርን?” አሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ