በዚህ ጊዜ ያዕቆብ እጅግ በመፍራት ተጨነቀ፤ አብረውት የነበሩትንም ሰዎች በሁለት ክፍል መደባቸው፤ እንዲሁም በጎቹን፥ ፍየሎቹን፥ ከብቶቹንና ግመሎቹን በሁለት በሁለት መደባቸው። ይህንንም ያደረገው “ዔሳው መጥቶ በድንገተኛ አደጋ የመጀመሪያውን ክፍል ቢያጠቃ፥ ሌላው ክፍል ሊያመልጥ ይችላል” ብሎ በማሰብ ነው። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅ አምላክ ሆይ! ልመናዬን አድምጥ፤ አምላክ ሆይ፥ ‘ወደ ትውልድ አገርህና ወደ ዘመዶችህ ተመለስ፤ እዚያም መልካም ነገር እንዲሆንልህ አደርጋለሁ’ ብለኸኝ ነበር። እኔ ባሪያህ ይህን ያኽል ቸርነትና ታማኝነት ልታሳየኝ የሚገባኝ አልነበርኩም፤ ዮርዳኖስን ተሻግሬ ስመጣ ከምመረኰዘው በትር በቀር ምንም አልነበረኝም፤ አሁን ግን እነዚህን በሁለት ቡድን የተከፈሉ ወገኖች ይዤ ተመልሻለሁ። በእኔ ላይ አደጋ በመጣል ሴቶችና ሕፃናት እንኳ ሳይቀሩ ያጠፋናል ብዬ ስለ ፈራሁ ከወንድሜ ከዔሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤ ‘መልካም ነገር አደርጋለሁ፤ ዘርህንም ሊቈጠር እንደማይቻል እንደ ባሕር ዳር አሸዋ አበዛልሃለሁ’ ያልከውን አስታውስ።” እዚያም ዐደረ፤ በማግስቱም ካለው ነገር ሁሉ ለወንድሙ ለዔሳው ስጦታ የሚሆን ነገር መርጦ አዘጋጀ፤ በዚህ ዐይነት ሁለት መቶ እንስት ፍየሎች፥ ኻያ ተባዕት ፍየሎች፥ ሁለት መቶ እንስት በጎች፥ ኻያ ተባዕት በጎች፤ ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎች ከነግልገሎቻቸው፥ አርባ ላሞች፥ ዐሥር ኰርማዎች፥ ኻያ እንስት አህዮችና ዐሥር ተባዕት አህዮች መረጠ፤ እነዚህንም በየመንጋው ከፈለና ለእያንዳንዳቸው እረኞች መደበላቸው፤ እረኞቹንም “ከእኔ ቀድማችሁ ሂዱ፤ በየመንጋው መካከል ርቀት እንዲኖር አድርጋችሁ፥ በመከታተል ሂዱ” አላቸው። የመጀመሪያዎቹንም እረኞች እንዲህ በማለት አዘዛቸው፤ “ወንድሜ ዔሳው በመንገድ አግኝቶ ‘የማን ሰዎች ናችሁ? ወዴትስ ትሄዳላችሁ? እነዚህ የምትነዱአቸው ከብቶች የማን ናቸው?’ ብሎ የጠየቃችሁ እንደ ሆነ፥ ‘እነዚህ ከብቶች የአገልጋይህ የያዕቆብ ናቸው፤ እርሱ እነዚህን የላከው ለጌታዬ ለዔሳው ስጦታ የሚሆን ነው፤ እነሆ ያዕቆብ ከኋላችን ነው’ ብላችሁ ንገሩት።” ለሁለተኛውም ለሦስተኛውም ክፍል እረኞችና ለቀሩትም የመንጋ ጠባቂዎች “እናንተም ዔሳውን ስታገኙት እንደዚሁ ንገሩት፤ ‘በተለይም አገልጋይህ ያዕቆብ ከበስተኋላ እየመጣ ነው’ ብላችሁ ንገሩት” አላቸው። ይህንንም ያለበት ምክንያት “እኔ ከመድረሴ በፊት በሚደርስለት ስጦታ ቊጣውን አበርድ ይሆናል፤ በኋላም በማገኘው ጊዜ በደስታ ይቀበለኛል” በሚል ሐሳብ ነው። በዚህ ዐይነት ስጦታውን አስቀድሞ ከላከ በኋላ፥ እዚያው በሰፈሩበት ቦታ ዐደረ።
ኦሪት ዘፍጥረት 32 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 32:7-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች