የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 3:8-24

ኦሪት ዘፍጥረት 3:8-24 አማ05

በመሸ ጊዜ፥ እግዚአብሔር አምላክ በአትክልቱ ቦታ ውስጥ ሲመላለስ ድምፁን ሰሙ፤ አዳምና ሚስቱ እግዚአብሔር አምላክ እንዳያያቸው በዛፎች መካከል ተደበቁ። ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ጠርቶ “የት ነው ያለኸው?” ሲል ጠየቀው። አዳምም “በአትክልቱ ቦታ ውስጥ የአንተን ድምፅ ሰማሁ፤ እራቁቴንም ስለ ሆንኩ በመፍራት ተደበቅሁ” አለ። እግዚአብሔርም “እራቁትህን እንደ ሆንክ ማን ነገረህ? አትብላ ካልኩህ ዛፍ ፍሬ ወስደህ በላህን?” አለው። አዳምም “ይህች አብራኝ እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት ፍሬውን ከዛፉ ወስዳ ሰጠችኝና በላሁ” አለ። እግዚአብሔር አምላክም ሴቲቱን “ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃት። እርስዋም “እባብ አታለለኝና በላሁ” አለች። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ እባቡን እንዲህ አለው፦ “ይህን በማድረግህ ከእንስሶችና ከአራዊት ሁሉ ተለይተህ የተረገምክ ሁን፤ ከዛሬ ጀምሮ በደረትህ እየተሳብክ ሂድ፤ ዕድሜህን ሙሉ ዐፈር ብላ፤ በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በአንተ ዘርና በእርስዋ ዘር መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ። የእርስዋ ዘር የአንተን ራስ ይቀጠቅጣል፤ አንተም የእርስዋን ዘር ተረከዝ ትነክሳለህ።” ሴቲቱንም፥ “በእርግዝናሽ ወራት ጭንቀትሽን፥ በምትወልጂበትም ጊዜ የምጥ ሥቃይሽን አበዛሁ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ፍላጎትሽ ለባልሽ ይሆናል። ለእርሱም ታዛዥ ትሆኚአለሽ” አላት። አዳምንም እንዲህ አለው፥ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ ‘አትብላ’ ያልኩህን ፍሬ ከዛፉ ወስደህ ስለ በላህ፥ አንተ በፈጸምከው ክፉ ሥራ ምክንያት ምድር የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህ ሁሉ ምግብህን ከእርስዋ የምትበላው በብርቱ ድካም ነው። ምድር እሾኽና አሜከላ ታበቅላለች፤ አንተም የዱር ተክሎችን ትበላለህ። ወደ መጣህበት ወደ መሬት እስክትመለስ ድረስ፥ እንጀራህን በግንባርህ ላብ ትበላለህ።” ዐፈር ነህና፥ ወደ ዐፈርም ትመለሳለህ። አዳምም ሚስቱ ሕይወት ላላቸው ሰብአዊ ፍጡሮች ሁሉ እናት ስለ ሆነች “ሔዋን” የሚል ስም አወጣላት። እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሔዋን ከቆዳ ልብስ ሠርቶ አለበሳቸው። እግዚአብሔር አምላክም እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ አዳም ክፉንና ደግን በማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ወስዶ በመብላት ለዘለዓለም እንዲኖር አይገባውም።” በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከዔደን የአትክልት ቦታ አስወጣው፤ የተገኘበትንም ምድር እንዲያለማ አደረገው። አዳምንም ካስወጣው በኋላ ከዔደን የአትክልት ቦታ በስተ ምሥራቅ በኩል ኪሩቤል የተባሉትን መላእክትንና በየአቅጣጫው እየተገለባበጠ እንደ እሳት የሚንበለበለውን ሰይፍ አኖረ፤ ይህንንም ያደረገው ማንም ወደ ሕይወት ዛፍ እንዳይጠጋ ነው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}