የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 3:8-24

ዘፍጥረት 3:8-24 NASV

ቀኑ መሸትሸት ሲል፣ እግዚአብሔር አምላክ በአትክልቱ ስፍራ ሲመላለስ አዳምና ሚስቱ ድምፁን ሰምተው ከእግዚአብሔር አምላክ ፊት በዛፎቹ መካከል ተሸሸጉ። እግዚአብሔር አምላክ ግን አዳምን ተጣርቶ፣ “የት ነህ?” አለው። አዳምም፣ “ድምፅህን በአትክልቱ ስፍራ ሰማሁ፤ ዕራቍቴን ስለ ሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔርም፣ “ዕራቍትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ‘ከርሱ እንዳትበላ’ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን?” አለው። አዳምም፣ “ይህች ከእኔ ጋራ እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት፣ እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ። እግዚአብሔር አምላክ ሴቲቱን፣ “ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?” አላት። እርሷም፣ “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” አለች። እግዚአብሔር አምላክ እባብን እንዲህ አለው፤ “ይህን ስለ ሠራህ፣ “ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉ ተለይተህ የተረገምህ ሁን፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፣ በደረትህ እየተሳብህ ትሄዳለህ፤ ዐፈርም ትበላለህ። በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” ሴቲቱንም እንዲህ አላት፤ “በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፤ በሥቃይም ትወልጃለሽ፤ ፍላጎትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፤ እርሱም የበላይሽ ይሆናል።” አዳምንም እንዲህ አለው፤ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ፣ ‘ከርሱ አትብላ’ ብዬ ያዘዝሁህን ዛፍ በልተሃልና፣ “ከአንተ የተነሣ ምድር የተረገመች ትሁን፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ምግብህን ጥረህ ግረህ ከርሷ ታገኛለህ። ምድርም እሾኽና አሜከላ ታበቅልብሃለች፤ ከቡቃያዋም ትበላለህ። ከምድር ስለ ተገኘህ፣ ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።” አዳምም የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ሚስቱን ሔዋን ብሎ ጠራት። እግዚአብሔር አምላክ ከቈዳ ልብስ አዘጋጅቶ አዳምንና ሚስቱን አለበሳቸው። ከዚያም እግዚአብሔር አምላክ፣ “ሰው መልካምንና ክፉውን ለይቶ በማወቅ ረገድ አሁን ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል፤ አሁን ደግሞ እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ቀጥፎ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም እንዳይኖር ይከልከል” አለ። ስለዚህ የተገኘበትን ምድር እንዲያርስ፣ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከዔድን የአትክልት ስፍራ አስወጣው፤ ሰውንም ካስወጣው በኋላ፣ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና በየአቅጣጫው የምትገለባበጥ ነበልባላዊ ሰይፍ ከዔድን በስተምሥራቅ አኖረ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}