ያዕቆብ ቤርሳቤህን ትቶ ወደ ካራን ለመሄድ ተነሣ፤ ፀሐይ በጠለቀች ጊዜ ወደ አንድ ስፍራ መጥቶ ዐረፈ፤ በዚያም አንድ ድንጋይ ተንተርሶ ተኛ፤ በሕልሙም ከመሬት እስከ ሰማይ የሚደርስ መሰላል አየ፤ በመሰላሉም የእግዚአብሔር መላእክት ወደ ላይ ይወጡና ወደ ታች ይወርዱ ነበር። እግዚአብሔርም በአጠገቡ ቆሞ እንዲህ አለው፤ “እኔ የአባትህ የአብርሃምና የይስሐቅ አምላክ እግዚአብሔር ነኝ፤ ለአንተና ለትውልድህ እንዲሆን ይህን የተኛህበትን ምድር እሰጥሃለሁ፤ ዘርህን እንደ ምድር አሸዋ አበዛዋለሁ፤ እነርሱ በሁሉ አቅጣጫ ይዞታቸውን ያስፋፋሉ፤ በአንተና በዘርህ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ይባረካሉ። አይዞህ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በምትሄድበትም ስፍራ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚህም ምድር በደኅና እመልስሃለሁ፤ የገባሁልህን ቃል ኪዳን ሁሉ እፈጽምልሃለሁ፤ ከቶም አልተውህም።” ያዕቆብም ከእንቅልፉ ነቃና “በእርግጥ እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ ግን ይህን አላወቅሁም ነበር” አለ። በጣም ፈርቶም ስለ ነበር “ይህ እንዴት የሚያስፈራ ቦታ ነው! ይህ የእግዚአብሔር ቤት መሆን አለበት፤ ወደ ሰማይ የሚያስገባው በር ይህ ነው” አለ። ያዕቆብ በማግሥቱ ጠዋት በማለዳ ተነሣ፤ ተንተርሶት የነበረውንም ድንጋይ መታሰቢያ እንዲሆን እንደ ሐውልት አቆመው፤ በላዩ ላይም የወይራ ዘይት አፈሰሰበት። ያንንም ስፍራ “ቤትኤል” ብሎ ሰየመው፤ ይህ ስፍራ ከዚያ በፊት ሎዛ እየተባለ ይጠራ ነበር። ከዚህ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ ለእግዚአብሔር ተሳለ፦ “ከእኔ ጋር ሆነህ በምሄድበት መንገድ ብትጠብቀኝ፥ የሚያስፈልገኝን ምግብና ልብስ ብትሰጠኝ፥ ወደ አባቴም ቤት በሰላም ብትመልሰኝ፥ አንተ አምላኬ ትሆናለህ፤ ይህ ለመታሰቢያነት ያቆምኩት ድንጋይ ወደ ፊት የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል፤ ከምትሰጠኝም ሁሉ ከዐሥር አንዱን እጅ ለአንተ እሰጣለሁ።”
ኦሪት ዘፍጥረት 28 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 28:10-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች