ዘፍጥረት 28:10-22

ዘፍጥረት 28:10-22 NASV

ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሥቶ ወደ ካራን ሄደ። ወደ አንድ ስፍራ እንደ ደረሰም ፀሓይዋ ጠልቃ ስለ ነበር፣ ዐዳሩን በዚያ አደረገ፤ በአቅራቢያው ከነበሩትም ድንጋዮች አንዱን ተንተርሶ ተኛ። በሕልሙም፣ ጫፉ ሰማይ የሚደርስ መሰላል በምድር ላይ ቆሞ፣ በላዩም የእግዚአብሔር መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ አየ። እግዚአብሔርም ከጫፉ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ፤ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ የተኛህበትን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ። ዘርህ እንደ ምድር አሸዋ ይበዛል፤ በምዕራብና በምሥራቅ፣ በሰሜንና በደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በአንተና በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ። እኔ ከአንተ ጋራ ነኝ፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የሰጠሁህን ተስፋ እስከምፈጽምልህ ድረስ አልተውህም።” ያዕቆብም ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ “በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ ግን ይህን አላወቅሁም ነበር” አለ። እርሱም በፍርሀት፣ “ይህ ስፍራ እንዴት የሚያስፈራ ነው! ይህስ ሌላ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቤት መሆን አለበት፤ የሰማይ ደጅ ነው” አለ። ያዕቆብም በማግስቱም ማልዶ ተነሣ፣ ተንተርሶት ያደረውን ድንጋይ አንሥቶ እንደ ሐውልት አቆመው፤ በዐናቱም ላይ የወይራ ዘይት አፈሰሰበት። ያን ቦታ ቤቴል ብሎ ሰየመው፤ ቀደም ሲል ግን የከተማዪቱ ስም ሎዛ ነበር። ከዚያም ያዕቆብ እንዲህ ሲል ተሳለ፤ “እግዚአብሔር ከእኔ ጋራ ቢሆን በምሄድበትም መንገድ ቢጠብቀኝ፣ የምበላው ምግብ፣ የምለብሰው ልብስ ቢሰጠኝ ወደ አባቴ ቤትም በደኅና ቢመልሰኝ፣ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆናል፤ ይህ ሐውልት አድርጌ ያቆምሁት ድንጋይ፣ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል፤ ከምትሰጠኝም ሀብት ሁሉ፣ ከዐሥር እጅ አንዱን ለአንተ እሰጣለሁ።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}