ኦሪት ዘፍጥረት 26:2-25

ኦሪት ዘፍጥረት 26:2-25 አማ05

በዚያም እግዚአብሔር ለይስሐቅ ተገለጠለትና እንዲህ አለው፤ “ወደ ግብጽ አገር አትሂድ፤ እንድትኖርበት በምነግርህ በዚህ ምድር ተቀመጥ፤ እዚሁ ኑር፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እባርክሃለሁም፤ ይህን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ፤ በዚህ ዐይነት ለአባትህ ለአብርሃም የገባሁትን ቃል ኪዳን እፈጽማለሁ፤ ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ይህንንም ሁሉ ምድር አወርሳቸዋለሁ፤ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ። አንተን የምባርክበትም ምክንያት አባትህ አብርሃም ለእኔ ታዛዥ በመሆን የሰጠሁትን ትእዛዞች፥ ድንጋጌዎችንና ሕጎችን ሁሉ ስለ ጠበቀ ነው።” ስለዚህ ይስሐቅ መኖሪያውን በገራር አደረገ፤ የዚያ አገር ሰዎችም ስለ ርብቃ “ምንህ ናት” ብለው በጠየቁት ጊዜ “እኅቴ ናት” አላቸው፤ ይህንንም ያለበት ምክንያት ርብቃ በጣም ቈንጆ ስለ ነበረች የዚያ አገር ሰዎች በእርስዋ ሰበብ እንዳይገድሉት በመፍራት ነው። ይስሐቅ እዚያ አገር ብዙ ጊዜ ከቈየ በኋላ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቤሜሌክ በመስኮት ወደ ውጪ ሲመለከት ይስሐቅና ርብቃ እንደ ባልና ሚስት በመዳራት ሲጫወቱ አየ፤ ስለዚህ አቤሜሌክ ይስሐቅን አስጠርቶ “ለካስ ርብቃ ሚስትህ ናት! ታዲያ ‘እኅቴ ናት’ ያልከው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። እርሱም “ሚስቴ ነች ያልኩ እንደሆን ሰዎች ይገድሉኛል ብዬ ስለ ፈራሁ ነው” ብሎ መለሰ። አቤሜሌክም “ይህ በእኛ ላይ ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው? ከእኛ ሰዎች አንዱ በቀላሉ ሚስትህን ለመድፈር በቻለ ነበር፤ እኛንም ኃጢአተኞች ልታደርገን ነበር፤” ቀጥሎም አቤሜሌክ “ይህን ሰው ወይም ሚስቱን የሚነካ ሰው በሞት ይቀጣል” የሚል ማስጠንቀቂያ ለሕዝቡ ሰጠ። ይስሐቅ በዚያች ምድር ዘርን ዘራ፤ እግዚአብሔር ስለ ባረከውም በዚያኑ ዓመት መቶ እጥፍ አመረተ፤ ሀብት በሀብት ላይ እየተጨመረለት ስለ ሄደ እጅግ ባለጸጋ ሆነ። ብዙ የበግና የከብት መንጋ፥ እንዲሁም ብዙ አገልጋዮች ስለ ነበሩት ፍልስጥኤማውያን ቀኑበት። ስለዚህ የይስሐቅ አባት አብርሃም በሕይወት በነበረበት ዘመን የእርሱ አገልጋዮች ቆፍረዋቸው የነበሩትን የውሃ ጒድጓዶች ሁሉ ዐፈር ሞልተው ደፈኑአቸው። በዚያን ጊዜ አቤሜሌክ ይስሐቅን “ኀይልህ ከእኛ ይልቅ እየበረታ ስለ ሄደ፥ አገራችንን ለቀህ ውጣ” አለው። በዚህ ምክንያት ይስሐቅ ያንን ቦታ ለቆ በገራር ሸለቆ ውስጥ ሰፈረ፤ እዚያም ተቀመጠ። አብርሃም በሕይወት ሳለ አስቈፍሮአቸው የነበሩትንና አብርሃም ከሞተ በኋላ ግን ፍልስጥኤማውያን የደፈኑአቸውን የውሃ ጒድጓዶች ይስሐቅ እንደገና እንዲቈፈሩ አደረገ፤ አባቱ ባወጣላቸው ስሞችም ጠራቸው። የይስሐቅ አገልጋዮች በሸለቆው ውስጥ የውሃ ጒድጓድ ቆፈሩና ጥሩ የምንጭ ውሃ አገኙ፤ የገራር እረኞች ግን “ይህ ውሃ የእኛ ነው” በማለት ከይስሐቅ እረኞች ጋር ተጣሉ። በዚህ ምክንያት ይስሐቅ ጒድጓዱን “ዔሤቅ” ብሎ ሰየመው። የይስሐቅ አገልጋዮች ሌላ የውሃ ጒድጓድ ቈፈሩ፤ በዚህኛውም ጒድጓድ ምክንያት ሌላ ጠብ ተነሣ፤ ስለዚህ ይስሐቅ ይህን ጒድጓድ “ስጥና” ብሎ ሰየመው። ከዚያም እልፍ ብሎ ሌላ የውሃ ጒድጓድ ቈፈረ፤ በዚህኛው የውሃ ጒድጓድ ምክንያት ምንም ጠብ ስላልተነሣ “እነሆ፥ አሁን እግዚአብሔር ሰፊ ቦታ ሰጠን፤ በምድር ላይም እንበዛለን ሲል፥ ያንን ቦታ ‘ረሖቦት’ ” ብሎ ሰየመው። ከዚህ በኋላ ይስሐቅ ወደ ቤርሳቤህ ወጣ፤ በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለትና “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ እኔ ከአንተ ጋር ስለ ሆንኩ አትፍራ፤ ለአገልጋዬ ለአብርሃም በገባሁት ቃል ኪዳን መሠረት እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም አበዛዋለሁ” አለው። ይስሐቅ በዚያ መሠዊያ ሠራና ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ መኖሪያውንም እዚያ አደረገ፤ አገልጋዮቹም ሌላ ጒድጓድ ቈፈሩ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}