ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፤ እግዚአብሔርም “አብርሃም!” ብሎ ጠራው፤ አብርሃምም “እነሆ፥ አለሁኝ!” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔርም “የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ እዚያ በማሳይህ አንድ ኮረብታ ላይ እርሱን መሥዋዕት አድርገህ አቅርብልኝ” አለው። አብርሃም ጠዋት በማለዳ ተነሥቶ ለመሥዋዕቱ የሚሆን እንጨት ቈረጠና በአህያው ላይ ጫነው፤ ከእርሱ ጋር ልጁን ይስሐቅንና ሁለት አገልጋዮችን ይዞ እግዚአብሔር ወዳመለከተው ቦታ ለመሄድ ጒዞ ጀመረ። በሦስተኛው ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ሲመለከት ቦታውን በሩቅ አየ። ከዚህ በኋላ አብርሃም አገልጋዮቹን “እናንተ ከአህያው ጋር እዚህ ቈዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ሄደን ለእግዚአብሔር ከሰገድን በኋላ እንመለሳለን” አላቸው። አብርሃምም የመሥዋዕቱን እንጨት አንሥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸከመው፤ እርሱ ግን ቢለዋውንና እሳቱን ያዘ፤ ሁለቱም አብረው ሲሄዱ ሳለ፥ ይስሐቅ አብርሃምን “አባባ!” አለው፤ አብርሃምም “እነሆ፥ አለሁ ልጄ!” አለው። ይስሐቅም “እነሆ፥ እሳትና እንጨት ይዘናል፤ ታዲያ ለመሥዋዕት የሚሆነው በግ የት አለ?” በማለት አብርሃምን ጠየቀው። አብርሃምም “ልጄ ሆይ፥ ለመሥዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ለራሱ ያዘጋጃል” አለው፤ ሁለቱም አብረው መንገዳቸውን ቀጠሉ። እግዚአብሔር ወዳመለከተው ቦታ በደረሱ ጊዜ አብርሃም መሠዊያ ሠርቶ እንጨቱን በላዩ ላይ ረበረበው፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ ከእንጨቱ በላይ በመሠዊያው ላይ አጋደመው። ልጁን ለማረድ ቢላዋ አንሥቶ እጁን ዘረጋ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ “አብርሃም! አብርሃም!” ብሎ ጠራው። አብርሃምም “እነሆ፥ አለሁኝ!” አለ። መልአኩም “ልጁን አትንካ፤ ምንም ዐይነት ጒዳት አታድርስበት፤ አንድ ልጅህን እንኳ ለእኔ ከመስጠት ስለ አልተቈጠብክ እነሆ፥ እኔን እግዚአብሔርን የምትፈራ መሆንህን ተረድቼአለሁ።”
ኦሪት ዘፍጥረት 22 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 22:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos