የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 22:1-12

ዘፍጥረት 22:1-12 NASV

ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፤ “አብርሃም!” አለው። እርሱም “አቤቱ አለሁ” አለ። እግዚአብሔርም፣ “የምትወድደውን አንዱን ልጅህን፣ ይሥሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ እኔ በማመለክትህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው” አለው። በማግስቱም ጧት አብርሃም ማልዶ ተነሣ፤ አህያውን ጭኖ፣ ሁለት አገልጋዮቹንና ልጁን ይሥሐቅን ይዞ፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚበቃውን ዕንጨት ከቈረጠ በኋላ እግዚአብሔር ወዳመለከተው ቦታ ለመሄድ ጕዞውን ጀመረ፤ በሦስተኛው ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ቦታውን ከሩቅ ተመለከተ፤ አገልጋዮቹንም “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቈዩን፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ ሄደን ለእግዚአብሔር ሰግደን እንመለሳለን” አላቸው። አብርሃም ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን ዕንጨት ወስዶ፣ ልጁን ይሥሐቅን አሸከመው፤ እሳቱንና ቢላዋውንም ራሱ ያዘ። ሁለቱም ዐብረው ሄዱ። ይሥሐቅም አባቱን አብርሃምን፣ “አባቴ ሆይ” አለው። አብርሃምም፣ “እነሆኝ፤ አለሁ ልጄ” አለው። ይሥሐቅም፣ “እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው፤ ነገር ግን የሚቃጠለው መሥዋዕት በግ የት አለ?” ብሎ ጠየቀ። አብርሃምም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለሚቃጠለው መሥዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል” አለው። ሁለቱም ዐብረው ጕዟቸውን ቀጠሉ። እግዚአብሔር ወደ አመለከተው ቦታ እንደ ደረሱ፣ አብርሃም መሠዊያ ሠራ፤ በላዩም ላይ ዕንጨት ረበረበ፤ ልጁን ይሥሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ዕንጨት ላይ አጋደመው። ከዚያም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላዋውን አነሣ። የእግዚአብሔር መልአክ ግን ከሰማይ፣ “አብርሃም! አብርሃም!” ብሎ ጠራው። አብርሃምም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ። እርሱም፣ “እጅህን በብላቴናው ላይ አታሳርፍ፤ ምንም ጕዳት አታድርስበት፤ እነሆ፤ እግዚአብሔርን እንደምትፈራ ተረድቻለሁ፤ ልጅህን፣ ያውም አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሣሣህምና” አለው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}