ኦሪት ዘፍጥረት 19:15-29

ኦሪት ዘፍጥረት 19:15-29 አማ05

በማግስቱ ጠዋት በማለዳ መላእክቱ ሎጥን “ፍጠን! ከተማይቱ ስትጠፋ አብራችሁ እንዳትጠፉ ሚስትህንና ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ይዘህ ከዚህ ውጣ” እያሉ አጣደፉት። ሎጥ ግን አመነታ፤ ሆኖም እግዚአብሔር ለእርሱና ለቤተሰቡ ስለ ራራ መላእክቱ ሎጥንና ሚስቱን፥ ሁለቱን ሴቶች ልጆቹን፥ እጆቻቸውን ይዘው ከከተማዋ እንዲያወጡአቸው አደረገ። ካወጡአቸውም በኋላ ከመላእክቱ አንዱ “ሕይወታችሁን አድኑ! ወደ ኋላ አትመልከቱ! በሸለቆው ውስጥ አትዘግዩ፤ እንዳትሞቱ ወደ ተራራው ሽሹ!” አላቸው። ሎጥ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ጌቶቼ፥ እባካችሁ ወደዚያ እንድንወጣ አታደርጉ፤ እኔ አገልጋያችሁ በፊታችሁ ሞገስ ስላገኘሁ ሕይወቴን ለማዳን ታላቅ ርዳታ አድርጋችሁልኛል፤ ነገር ግን ይህ ጥፋት ደርሶብኝ እሞታለሁ ብዬ ስለምሰጋ ወደዚያ ተራራ መሸሽ አልችልም። እኔ በፍጥነት ሸሽቼ ላመልጥበት የምችል እነሆ አንዲት ትንሽ ከተማ በቅርብ አለች፤ ስለዚህ ሸሽቼ ወደ እርሷ እንድሄድ ፍቀዱልኝ፤ እንደምታዩአት ትንሽ ከተማ ናት፤ ወደ እርስዋ ብሄድ ሕይወቴ ከጥፋት ይድናል።” መልአኩም “እሺ አንተ ባልከው እስማማለሁ፤ ይህችን አንተ የምትላትን ከተማ አላጠፋትም፤ ወደዚያች ከተማ እስከምትደርስ ምንም ማድረግ ስለማልችል ፈጥነህ ወደ እርስዋ ሽሽ!” አለው። ሎጥ ያቺን ከተማ ትንሽ ብሎአት ስለ ነበር ጾዓር ተባለች። ሎጥ ወደ ጾዓር ሲደርስ ገና ፀሐይ መውጣትዋ ነበር፤ እግዚአብሔር በሰዶምና በገሞራ ከተሞች ላይ እሳትና ዲን ከራሱ (ከእግዚአብሔር ዘንድ) ከሰማይ አዘነበ። በዚህ ዐይነት እነዚያን ከተሞችና ሸለቆዎች፥ እዚያ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ፥ በምድሩም ላይ የበቀለውን ነገር ሁሉ ደመሰሰ። የሎጥ ሚስትም ወደ ኋላዋ ስለ ተመለከተች የጨው ዐምድ ሆና ቀረች። አብርሃም በማግስቱ ማለዳ ተነሥቶ ከዚህ ቀደም ከእግዚአብሔር ጋር ወደተገናኘበት ቦታ ሄደ። ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ ወደ ሸለቆውም ቊልቊል በተመለከተ ጊዜ ከታላቅ ምድጃ እንደሚወጣ ጢስ ከባድ የእሳት ጢስ ከዚያ ሲወጣ አየ። ሎጥ ይኖርባቸው የነበሩትን፥ በሸለቆ የሚገኙትን ከተሞች፥ እግዚአብሔር ባጠፋ ጊዜ አብርሃምን አስታወሰ፤ ስለዚህም ሎጥን ከጥፋት ወደሚድንበት ቦታ መራው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}