በዚያኑ ምሽት ሁለቱ መላእክት ወደ ሰዶም መጡ፤ በዚያን ጊዜ ሎጥ በከተማይቱ በር ተቀምጦ ነበር፤ መላእክቱን ባያቸው ጊዜ ሊያነጋግራቸው ከተቀመጠበት ተነሥቶ ሄደ፤ ጐንበስ ብሎም እጅ ነሣቸውና፥ “ጌቶቼ ሆይ፥ ተቀብዬ ላስተናግዳችሁ ዝግጁ ነኝ፤ እባካችሁ ወደ ቤቴ ግቡ፤ እግራችሁንም ታጥባችሁ እዚሁ ዕደሩ፤ ጠዋት በማለዳ ተነሥታችሁ ጒዞአችሁን ትቀጥላላችሁ” አላቸው። እነርሱ ግን “አይሆንም፤ እኛ እዚሁ በከተማይቱ አደባባይ እናድራለን” አሉት። ነገር ግን ወደ ቤቱ እንዲገቡ አጥብቆ ስለ ለመናቸው፥ ከእርሱ ጋር ወደ ቤቱ ገቡ፤ ከዚህም በኋላ ሎጥ እንጀራ ጋግረው መልካም ራት እንዲያዘጋጁ ለአገልጋዮቹ ነገራቸው፤ ራትም በተዘጋጀ ጊዜ እንግዶቹ በሉ። እንግዶቹ ከመተኛታቸው በፊት የሰዶም ሰዎች ቤቱን ከበቡት፤ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ሳይቀሩ የከተማይቱ ወንዶች ሁሉ እዚያ ተሰበሰቡ። ሎጥንም ጠርተው “ከአንተ ጋር ለማደር ወደዚህ የገቡት ሰዎች የት አሉ? ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ለማድረግ ስለምንፈልግ ወደ እኛ አውጣቸው!” አሉት። ሎጥ ግን ወደ ውጪ ወጥቶ በሩን ከበስተኋላው ዘጋው፤ እንዲህም አላቸው “ወዳጆቼ ሆይ፥ እባካችሁ ይህን ክፉ ነገር አታድርጉ! እነሆ፥ ሁለት ያላገቡ ሴቶች ልጆች አሉኝ፤ እነርሱን ወደ እናንተ ላምጣላችሁና በእነርሱ ላይ የፈለጋችሁትን ነገር አድርጉ፤ በእነዚህ ሰዎች ግን ምንም ነገር አታድርጉ፤ እነርሱ የእኔ እንግዶች ስለ ሆኑ ልጠነቀቅላቸው ይገባኛል።” ሰዎቹ ግን “አንተ ስደተኛ፥ ሂድ ወዲያ! ለመሆኑ ልናደርገው የሚገባንን ነገር የምትነግረን አንተ ማን ነህ? ሂድ ወዲያ፤ አለበለዚያ በእነርሱ ላይ ልናደርግ ካሰብነው የከፋ ነገር በአንተ ላይ እናደርጋለን” አሉት። በዚህ ዐይነት ሎጥን ወዲያ ገፍትረው በሩን ለመስበር ተነሣሡ፤ ከቤቱ ውስጥ ያሉት ሁለቱ እንግዶች ግን እጆቻቸውን ወደ ውጪ አውጥተው ሎጥን ስበው ወደ ቤቱ ውስጥ አስገቡትና በሩን ዘጉ። ከዚያ በኋላ ውጪ የነበሩት ወጣቶችና ሽማግሌዎች ሁሉ በሩን ማየት እንዳይችሉ ዐይናቸውን አሳወሩአቸው። ሁለቱም እንግዶች ሎጥን እንዲህ አሉት፤ “በዚህች ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፥ የልጆችህ እጮኛዎችና ሌሎች ዘመዶች ቢኖሩህ ከዚህች ከተማ በፍጥነት እንዲወጡ አድርግ፤ ይህችን ከተማ ልናጠፋት ነው፤ የእነዚህ ሰዎች ኃጢአት እጅግ መብዛቱን እግዚአብሔር ሰምቶአል፤ ሰዶምንም እንድናጠፋ ልኮናል።” ከዚህ በኋላ ሎጥ ሴቶች ልጆቹን ወዳጩአቸው ሰዎች ቤት ሄደና “ቶሎ ብላችሁ ከዚህ ውጡ፤ እግዚአብሔር ይህን ስፍራ ሊደመስሰው ነው” አላቸው፤ እነርሱ ግን የሚቀልድ መስሎአቸው ቸል አሉ። በማግስቱ ጠዋት በማለዳ መላእክቱ ሎጥን “ፍጠን! ከተማይቱ ስትጠፋ አብራችሁ እንዳትጠፉ ሚስትህንና ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ይዘህ ከዚህ ውጣ” እያሉ አጣደፉት። ሎጥ ግን አመነታ፤ ሆኖም እግዚአብሔር ለእርሱና ለቤተሰቡ ስለ ራራ መላእክቱ ሎጥንና ሚስቱን፥ ሁለቱን ሴቶች ልጆቹን፥ እጆቻቸውን ይዘው ከከተማዋ እንዲያወጡአቸው አደረገ። ካወጡአቸውም በኋላ ከመላእክቱ አንዱ “ሕይወታችሁን አድኑ! ወደ ኋላ አትመልከቱ! በሸለቆው ውስጥ አትዘግዩ፤ እንዳትሞቱ ወደ ተራራው ሽሹ!” አላቸው። ሎጥ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ጌቶቼ፥ እባካችሁ ወደዚያ እንድንወጣ አታደርጉ፤ እኔ አገልጋያችሁ በፊታችሁ ሞገስ ስላገኘሁ ሕይወቴን ለማዳን ታላቅ ርዳታ አድርጋችሁልኛል፤ ነገር ግን ይህ ጥፋት ደርሶብኝ እሞታለሁ ብዬ ስለምሰጋ ወደዚያ ተራራ መሸሽ አልችልም። እኔ በፍጥነት ሸሽቼ ላመልጥበት የምችል እነሆ አንዲት ትንሽ ከተማ በቅርብ አለች፤ ስለዚህ ሸሽቼ ወደ እርሷ እንድሄድ ፍቀዱልኝ፤ እንደምታዩአት ትንሽ ከተማ ናት፤ ወደ እርስዋ ብሄድ ሕይወቴ ከጥፋት ይድናል።” መልአኩም “እሺ አንተ ባልከው እስማማለሁ፤ ይህችን አንተ የምትላትን ከተማ አላጠፋትም፤ ወደዚያች ከተማ እስከምትደርስ ምንም ማድረግ ስለማልችል ፈጥነህ ወደ እርስዋ ሽሽ!” አለው። ሎጥ ያቺን ከተማ ትንሽ ብሎአት ስለ ነበር ጾዓር ተባለች። ሎጥ ወደ ጾዓር ሲደርስ ገና ፀሐይ መውጣትዋ ነበር፤ እግዚአብሔር በሰዶምና በገሞራ ከተሞች ላይ እሳትና ዲን ከራሱ (ከእግዚአብሔር ዘንድ) ከሰማይ አዘነበ። በዚህ ዐይነት እነዚያን ከተሞችና ሸለቆዎች፥ እዚያ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ፥ በምድሩም ላይ የበቀለውን ነገር ሁሉ ደመሰሰ። የሎጥ ሚስትም ወደ ኋላዋ ስለ ተመለከተች የጨው ዐምድ ሆና ቀረች። አብርሃም በማግስቱ ማለዳ ተነሥቶ ከዚህ ቀደም ከእግዚአብሔር ጋር ወደተገናኘበት ቦታ ሄደ። ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ ወደ ሸለቆውም ቊልቊል በተመለከተ ጊዜ ከታላቅ ምድጃ እንደሚወጣ ጢስ ከባድ የእሳት ጢስ ከዚያ ሲወጣ አየ። ሎጥ ይኖርባቸው የነበሩትን፥ በሸለቆ የሚገኙትን ከተሞች፥ እግዚአብሔር ባጠፋ ጊዜ አብርሃምን አስታወሰ፤ ስለዚህም ሎጥን ከጥፋት ወደሚድንበት ቦታ መራው። ሎጥ በጾዓር መቀመጥ ስለ ፈራ እርሱና ሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ወደ ተራራዎቹ ወጥተው መኖሪያቸውን በዋሻ ውስጥ አደረጉ። አንድ ቀን ታላቂቱ ልጁ እኅትዋን እንዲህ አለቻት፦ “አባታችን ማርጀቱ ነው፤ ልጆች እንድንወልድ እኛን የሚያገቡ ወንዶች በዙሪያችን የሉም፤ ከእርሱ ጋር ተኝተን ከእርሱ ልጆች እንድናገኝ አባታችንን የወይን ጠጅ አጠጥተን እናስክረው።” በዚያን ምሽት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጥተው አሰከሩት፤ ታላቂቱ ልጁም ከእርሱ ጋር ግንኙነት አደረገች። ሎጥ ግን በጣም ሰክሮ ስለ ነበር ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም። በማግስቱ ታላቂቱ ልጅ እኅቷን “ትናንት ማታ እኔ ከእርሱ ጋር ተኝቼአለሁ፤ ዛሬም እንደገና የወይን ጠጅ አጠጥተን እናስክረውና አንቺም አብረሽው ተኚ፤ በዚህ ዐይነት ሁለታችንም ከአባታችን ልጆች ወልደን ዘራችን እንዳይጠፋ እናድርግ” አለቻት። ስለዚህ በዚያን ምሽት አባታቸውን እንደገና የወይን ጠጅ አጠጥተው አሰከሩት፤ ታናሽቱ ልጁም ከእርሱ ጋር ግንኙነት አደረገች፤ አሁንም እጅግ ሰክሮ ስለ ነበር ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም። በዚህ ሁኔታ ሁለቱም የሎጥ ሴቶች ልጆች ከአባታቸው ፀነሱ። ታላቂቱ ወንድ ልጅ ወለደችና ስሙን ሞአብ አለችው፤ እርሱ ዛሬ ሞአባውያን ተብለው ለሚጠሩት ሕዝቦች ቅድመ አያት ነው። ታናሽቱም ወንድ ልጅ ወለደችና ስሙን ቤንዐሚ አለችው፤ እርሱ ዛሬ ዐሞናውያን ተብለው ለሚጠሩት ሕዝቦች ቅድመ አያት ነው።
ኦሪት ዘፍጥረት 19 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 19:1-38
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች