ኦሪት ዘፍጥረት 18:1-14

ኦሪት ዘፍጥረት 18:1-14 አማ05

በመምሬ የወርካ ዛፎች አጠገብ እግዚአብሔር ለአብርሃም ተገለጠለት፤ የተገለጠለትም በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ከዕለታት አንድ ቀን በቀትር ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ነበር፤ ቀና ብሎም ሲመለከት ሦስት ሰዎች እዚያ ቆመው አየ፤ እንዳያቸውም ወዲያውኑ ሊያነጋግራቸው ወደ እነርሱ ሮጠ፤ ግንባሩም መሬት እስኪነካ ዝቅ ብሎ በመስገድ እጅ ነሣ፤ እንዲህም አለ፤ “ጌታዬ ሆይ፥ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ አልፈኸኝ እንዳትሄድ እለምንሃለሁ፤ እግራችሁን የምትታጠቡበት ውሃ እስካመጣላችሁ ድረስ በዚህ ዛፍ ጥላ ሥር ዐረፍ በሉ፤ ወደ እኔ ወደ አገልጋያችሁ በመምጣታችሁ ደስ ብሎኛል፤ ስለዚህ ለጒዞአችሁ ብርታት የሚሰጣችሁን ጥቂት ምግብ አምጥቼ እንዳስተናግዳችሁ ፍቀዱልኝ።” እነርሱም “መልካም ነው፤ እንዳልከው አድርግ” አሉት። አብርሃም ወደ ድንኳኑ ሮጦ ሄደና ሣራን “ቶሎ ብለሽ ሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውሰጂና አቡክተሽ እንጀራ ጋግሪ” አላት። ከዚህ በኋላ አብርሃም ወደ መንጋው ሄደና ለግላጋውንና መልካሙን ጥጃ መርጦ ለአገልጋዩ ሰጠው፤ አገልጋዩም በፍጥነት ዐርዶ አወራርዶ አዘጋጀው፤ አብርሃም እርጎ፥ ወተትና ሥጋ ይዞ ሄደና ምግቡን ለእንግዶቹ አቀረበላቸው፤ እነርሱ ምግቡን በሚበሉበት ጊዜ አብርሃም ከዛፉ ሥር አጠገባቸው ቆሞ ያስተናግዳቸው ነበር። እነርሱም “ሚስትህ ሣራ የት አለች?” አሉት። እርሱም “እዚያ ድንኳኑ ውስጥ ነች” አላቸው። ከሦስቱም እንግዶች አንዱ አብርሃምን “የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ፤ በዚያን ጊዜ ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው። እርሱም ይህን በሚናገርበት ጊዜ ሣራ በስተኋላው በድንኳኑ ደጃፍ ቆማ ታዳምጥ ነበር፤ አብርሃምና ሣራ በዕድሜአቸው መግፋት አርጅተው ነበር፤ የሣራም፥ ልጅ የመውለጃ ዕድሜዋ አልፎ ነበር። ስለዚህ ሣራ “እኔ አሁን እንዲህ ካረጀሁ በኋላ ጌታዬ አብርሃምም ካረጀ በኋላ እንዲህ ያለ ደስታ ሊኖረኝ ይችላልን?” ብላ በማሰብ ሳቀች። እግዚአብሔርም አብርሃምን “ሣራ ‘እንደዚህ ካረጀሁ በኋላ ልጅ መውለድ እችላለሁን’ በማለት ስለምን ሳቀች? ከቶ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? እንደ ነገርኩህ የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ፤ በዚያን ጊዜ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}