በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ አምራፌል፥ የኤላሳር ንጉሥ አርዮክ፥ የዔላም ንጉሥ ከዶርላዖሜር፥ የጎይም ንጉሥ ቲድዓል ነበሩ፤ እነዚህ አራቱ ነገሥታት፥ ሌሎችን አምስት ነገሥታት ለመውጋት ሄዱ፤ የተዘመተባቸውም አምስት ነገሥታት የሰዶም ንጉሥ ቤራዕ፥ የገሞራ ንጉሥ ቢርሻዕ፥ የአዳማ ንጉሥ ሺንአብ፥ የጸቦይም ንጉሥ ሼሜቤርና ጾዓር ተብላ የምትጠራው የቤላዕ ንጉሥ ነበሩ። እነዚህ ነገሥታት አንድ ግንባር ፈጥረው አሁን ሙት ባሕር ተብሎ በሚጠራው በሲዲም ሸለቆ ጦርነት ገጠሙ፤ እነዚህ ነገሥታት ለዐሥራ ሁለት ዓመት በከዶርላዖሜር ቊጥጥር ውስጥ ነበሩ፤ በዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ግን በእርሱ ላይ ዐመፁ። በዐሥራ አራተኛው ዓመት ከዶርላዖሜርና ከእርሱ ጋር የተባበሩት ነገሥታት ከነሠራዊቶቻቸው መጥተው ረፋያውያንን በዐስታሮት ቃርናይም፥ ዙዛውያንን በሃም፥ ኤማውያንን በሻዌ ቂርያታይም፥ የሖር ሰዎችንም በተራራማው አገር በኤዶም፥ በበረሓ አጠገብ እስካለው እስከ ኤልፋራን ባለው ስፍራ ድል ነሡአቸው። ከዚያም ተመልሰው ወደ ቃዴስ መጡ፤ በዚያን ጊዜ የዚህ ቦታ ስም ዔይንሚሽፖጥ ይባል ነበር። የዐማሌቃውያንንም ምድር ሁሉ ያዙ፤ በሐጸጾን ታማር ይኖሩ የነበሩትን አሞራውያንንም አሸነፉ። ከዚህ በኋላ የሰዶም፥ የገሞራ፥ የአዳማ፥ የጸቦይምና የቤላዕ ነገሥታት ሠራዊታቸውን በሲዲም ሸለቆ አሰልፈው ተዋጉ፤ የተዋጉትም ከዔላም፥ ከጎይም፥ ከባቢሎንና ከኤላሳር ነገሥታት ጋር ነበር፤ አምስቱ ነገሥታት ከአራቱ ነገሥታት ጋር የተዋጉት በዚህ ዐይነት ነበር። በሲዲም ሸለቆ ብዙ የቅጥራን ጒድጓዶች ነበሩ፤ ስለዚህ የሰዶምና የገሞራ ነገሥታት ከጦርነቱ ሸሽተው ለማምለጥ በሞከሩ ጊዜ በጒድጓዶቹ ውስጥ ወደቁ፤ የቀሩት ሦስት ነገሥታት ግን ወደ ተራራዎቹ ሸሹ። አራቱ ነገሥታት በሰዶምና በገሞራ ያገኙትን ነገር ሁሉ ምግብ እንኳ ሳይቀር ማርከው ሄዱ። የአብራም የወንድም ልጅ ሎጥ በሰዶም ይኖር ስለ ነበር እርሱን ማርከው፥ ሀብቱንም ሁሉ ይዘው ሄዱ። ነገር ግን አንድ ሰው ሸሽቶ መጣና የሆነውን ሁሉ ለዕብራዊው ለአብራም ነገረው፤ በዚያን ጊዜ አብራም የሚኖረው በአሞራዊው መምሬ የተቀደሱ የወርካ ዛፎች አጠገብ ነበር፤ መምሬና ወንድሞቹ ኤሽኮል፥ ዐኔር የአብራም የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞች ነበሩ። አብራም የወንድሙ ልጅ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ በቤቱ ተወልደው የጦር ልምምድ ያላቸውን 318 ሰዎች በትጥቅ አደራጅቶ አራቱን ነገሥታት በመከታተል እስከ ዳን ድረስ ሄደ። እዚያ ሰዎቹን በቡድን ከፋፍሎ እርሱና አገልጋዮቹ ከጠላቶቹ ጋር በሌሊት ጦርነት ገጥመው ድል አደረጋቸው፤ ከደማስቆ በስተሰሜን እስከሚገኘው እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። የተወሰደውንም ምርኮ ሁሉ መልሶ አመጣ፤ እንዲሁም የወንድሙን ልጅ ሎጥን ከነሀብቱ መልሶ አመጣ፤ ከእነርሱም ጋር ሴቶችና ሌሎች እስረኞች ነበሩ። አብራም ከዶርላዖሜርና ከእነርሱ ጋር አብረው የነበሩትን ነገሥታት ድል አድርጎ ሲመለስ፥ የሰዶም ንጉሥ “የንጉሥ ሸለቆ” እየተባለ በሚጠራው በሻዌህ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ፤ የልዑል እግዚአብሔር ካህን የነበረው የሳሌም ንጉሥ መልከጼዴቅም ለአብራም እንጀራና የወይን ጠጅ አመጣለት፤ እንዲህ ብሎም አብራምን ባረከው፤ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ልዑል እግዚአብሔር አብራምን ይባርክ! በጠላቶችህ ላይ ድልን ያቀዳጀህ፥ ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።” አብራምም በምርኮ ካገኘው ሀብት ሁሉ አንድ ዐሥረኛውን ለመልከ ጼዴቅ ሰጠው። የሰዶምም ንጉሥ አብራምን “በምርኮ ያገኘኸውን ሀብት ሁሉ ለራስህ ውሰድ፤ ሰዎቼን ግን መልስልኝ” አለው። አብራምም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ሰማይንና ምድርን በፈጠረ በልዑል እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ አንተ ‘አብራምን ሀብታም ያደረግኹት እኔ ነኝ’ እንዳትል ሌላው ቀርቶ አንዲት ክር ወይም የጫማ ማሰሪያ እንኳ ከአንተ አልወስድም። ስለዚህ ለራሴ ምንም ነገር አልወስድም፤ የእኔ ሰዎች የያዙትን እንዲወስዱ እስማማለሁ፤ እንዲሁም የጦር ቃል ኪዳን ጓደኞቼ ዐኔር፥ ኤሽኮልና መምሬ ድርሻቸውን ይውሰዱ።”
ኦሪት ዘፍጥረት 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 14:1-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች