ዘፍጥረት 14:1-24

ዘፍጥረት 14:1-24 NASV

አምራፌል የሰናዖር ንጉሥ፣ አርዮክ የእላሳር ንጉሥ፣ ኮሎዶጎምር የኤላም ንጉሥ፣ ቲድዓል የጎይም ንጉሥ በነበሩበት ዘመን፣ ከሰዶም ንጉሥ ከበላ፣ ከገሞራ ንጉሥ ከብርሳ፣ ከአዳማ ንጉሥ ከሰነአብ፣ ከስቦይ ንጉሥ ከሰሜበር፣ እንዲሁም ዞዓር ከተባለች ከቤላ ንጉሥ ጋራ ለመዋጋት ወጡ። እነዚህ የኋለኞቹ ዐምስቱ ነገሥታት በሲዲም ሸለቆ፣ በጨው ባሕር ተሰበሰቡ። እነርሱም ዐሥራ ሁለት ዓመት ለኮሎዶጎምር ከተገዙ በኋላ በዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ዐመፁ። በዐሥራ አራተኛው ዓመት ኮሎዶጎምርና ከርሱ ጋራ የተባበሩት ነገሥታት ወጡ፤ ራፋይምን በአስጣሮት ቃርናይም፣ ዙዚምን በሃም፣ ኤሚማውያን በሴዊ ቂርያታይም፣ የሖሪ ሰዎችንም በተራራማው አገር በሴይር በረሓማ አጠገብ እስካለው እስከ ኤልፋራን ድረስ ድል አደረጓቸው። ከዚያም ተመልሰው ዓይንሚስፖጥ ወደተባለው ወደ ቃዴስ መጡ፤ የአማሌቃውያንና በሐሴሶን ታማር ይኖሩ የነበሩትን የአሞራውያንን ግዛት በሙሉ ድል አድርገው ያዙ። ከዚያም የሰዶም፣ የገሞራ፣ የአዳማ፣ የስቦይ እንዲሁም ዞዓር የተባለችው የቤላ ነገሥታት በሲዲም ሸለቆ ሰራዊታቸውን አስተባበሩ። እነዚህ ዐምስቱ፣ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎምር፣ በጎይም ንጉሥ በቲድዓል፣ በሰናዖር ንጉሥ በአምራፌል፣ በእላሳር ንጉሥ በአርዮክ፣ በእነዚህ በአራቱ ላይ ዘመቱባቸው። በሲዲም ሸለቆ ብዙ የቅጥራን ጕድጓዶች ስለ ነበሩ የሰዶምና የገሞራ ነገሥታት ሲሸሹ ከሰዎቻቸው አንዳንዶቹ በእነዚህ ጕድጓዶች ውስጥ ወደቁ፤ የቀሩትም ወደ ተራሮች ሸሹ። አራቱ ነገሥታትም በሰዶምና በገሞራ ያገኙትን ሀብትና ምግብ ሁሉ ዘርፈው ሄዱ። የአብራም ወንድም ልጅ ሎጥ፣ ሰዶም ይኖር ስለ ነበር እርሱንም ማርከው ንብረቱንም ዘርፈው ሄዱ። ከዚህም ያመለጠ አንድ ሰው መጥቶ ለዕብራዊው ለአብራም ይህን ነገረ፤ አብራም በዚያ ጊዜ ይኖር የነበረው በአሞራዊው መምሬ ታላላቅ ዛፎች አጠገብ ነበር። መምሬ፣ ወንድሞቹ ኤስኮልና አውናን የአብራም የኪዳን አጋሮቹ ነበሩ። አብራም የወንድሙን ልጅ መማረክ እንደ ሰማ በቤቱ ተወልደው አድገው የሠለጠኑ 318 ጦረኞች አሰልፎ እስከ ዳን ድረስ ገሠገሠ። አብራም ጠላቶቹን ለማጥቃት ሰራዊቱን ሌሊቱን በቡድን በቡድን ከፋፍሎ ከደማስቆ በስተሰሜን እስከሚገኘው እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። አብራም ጠላት የማረከውን በሙሉ አስጣለ፤ የወንድሙን ልጅ ሎጥን፣ ንብረቱን እንዲሁም ሴቶቹንና ሌሎቹን ምርኮኞች አስመለሰ። አብራም ኮሎዶጎምርንና ዐብረውት የተሰለፉትን ነገሥታት ድል አድርጎ ሲመለስ፣ የሰዶም ንጉሥ፣ “የንጉሥ ሸለቆ” ተብሎ በሚጠራው በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። የልዑል አምላክ ካህን የነበረው የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራና የወይን ጠጅ ይዞ ወጣ፤ አብራምንም እንዲህ ሲል ባረከው፤ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ልዑል አምላክ አብራምን ይባርክ፤ ጠላቶችህን አሳልፎ በእጅህ የሰጠህ፣ ልዑል አምላክ ይባረክ።” አብራምም ከሁሉ ነገር ዐሥራትን አውጥቶ ሰጠው። የሰዶም ንጉሥም አብራምን፣ “ሰዎቹን ለእኔ ስጠኝ፤ ንብረቱን ግን ለራስህ አስቀር” አለው። አብራም ግን ለሰዶም ንጉሥ እንዲህ አለው፤ “ሰማይንና ምድርን ወደ ፈጠረ ወደ እግዚአብሔር፣ ወደ ልዑል አምላክ እጆቼን አንሥቻለሁ፤ ‘አብራምን አበለጸግሁት’ እንዳትል፣ ብጣሽ ክርም ሆነ የጫማ ማሰሪያ እንኳ ከአንተ አንዳች አልፈልግም። ሰዎቼ ከበሉትና ከእኔ ጋራ ከሄዱት ሰዎች ድርሻ በቀር ለራሴ አንዳች ነገር አልቀበልም፤ አውናን፣ ኤስኮልና መምሬ ድርሻቸውን ይውሰዱ።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}