ከዚህ በኋላ አብራም ሎጥን እንዲህ አለው፤ “እኛ ወንድማማች ስለ ሆንን በእኔና በአንተ መካከል እንዲሁም በእኔ እረኞችና በአንተ እረኞች መካከል ጠብ ሊነሣ አይገባም፤ ምድሪቱ ሁሉ በፊትህ አይደለችምን? ከእኔ ተለይተህ ሂድ፤ አንተ ወደ ግራ ብትሄድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ ወይም አንተ ወደ ቀኝ ብትሄድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ።” ሎጥ ዙሪያውን በተመለከተ ጊዜ የዮርዳኖስ ሸለቆ እስከ ጾዓር ድረስ እንደ እግዚአብሔር ገነት ወይም እንደ ግብጽ ምድር ውሃ የሞላበት መሆኑን አየ፤ ይህን የተመለከተው እግዚአብሔር የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ከማጥፋቱ በፊት ነበር። ስለዚህ ሎጥ መላውን የዮርዳኖስን ሸለቆ ለራሱ መረጠና ወደ ምሥራቅ ሄደ፤ ሁለቱ የተለያዩት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ አብራም በከነዓን ኖረ፤ ሎጥ ግን በሸለቆው ውስጥ ባሉት ከተሞች መካከል ተቀመጠ፤ በሰዶምም አጠገብ ድንኳኑን ተከለ፤ በዚያን ዘመን የሰዶም ሰዎች እጅግ ክፉዎችና እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑ ኃጢአተኞች ነበሩ። ሎጥ ከሄደ በኋላ እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ አለው፤ “ካለህበት ስፍራ ሆነህ ወደ ሰሜን፥ ወደ ደቡብ፥ ወደ ምሥራቅና ምዕራብ ተመልከት፤ ይህን የምታየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ እሰጣችኋለሁ፤ ለዘለዓለምም የእናንተ ይሆናል፤ ዘርህን እንደ ምድር አሸዋ አበዛዋለሁ፤ የምድር አሸዋ ሊቈጠር እንደማይቻል ሁሉ የአንተም ዘር እንዲሁ ሊቈጠር የማይቻል ይሆናል። ተነሥተህ በምድሪቱ ስፋትና ርዝመት ሂድ፤ ሁሉንም ለአንተ እሰጥሃለሁ።” ስለዚህ አብራም ድንኳኑን ነቅሎ በኬብሮን የመምሬ የተቀደሱ የወርካ ዛፎች ወደአሉበት ስፍራ ለመኖር ሄደ፤ እዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።
ኦሪት ዘፍጥረት 13 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 13:8-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች