አብራምም ሎጥን እንዲህ አለው፤ “እኛ ወንድማማቾች ነንና፣ በአንተና በእኔ ወይም በእረኞቻችን መካከል ጠብ ሊኖር አይገባም። ይኸው እንደምታየው አገሩ ሰፊ ነው፤ ብንለያይ ይሻላል። አንተ ግራውን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተ ቀኙን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ግራ አመራለሁ።” ሎጥ ዐይኑን አቅንቶ ሲመለከት፣ የዮርዳኖስ ረባዳ ሜዳ እንደ እግዚአብሔር ገነት፣ በዞዓር አቅጣጫ እንዳለው እንደ ግብጽ ምድር ውሃማ ቦታ ሆኖ አገኘው። እንዲህም የነበረው እግዚአብሔር የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ከማጥፋቱ በፊት ነው። ሎጥ የዮርዳኖስን ረባዳ ሜዳ በሙሉ መርጦ ወደ ምሥራቅ አመራ፤ ሁለቱ ሰዎች በዚሁ ተለያዩ። አብራም መኖሪያውን በከነዓን ምድር አደረገ፤ ሎጥ ግን በረባዳው ሜዳ ውስጥ ባሉት ከተሞች መካከል በሰዶም አቅራቢያ ድንኳኑን ተከለ። የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጥኣን ነበሩ። ሎጥ ከተለየው በኋላ እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ አለው፤ “ካለህበት ስፍራ ቀና ብለህ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ተመልከት፤ ዐይንህ የሚያየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁ። ዘርህን እንደ ምድር ትቢያ አበዛዋለሁ፤ ማንም የምድርን ትቢያ ሊቈጥር እንደማይችል ሁሉ የአንተም ዘር የማይቈጠር ይሆናል። እንግዲህ ምድሪቱን ስለምሰጥህ ተነሣ፤ በርዝመቷም፣ በስፋቷም ተመላለስባት።” አብራምም ድንኳኑን ነቀለ፤ ሄዶም ኬብሮን በሚገኙት ትልልቅ የመምሬ ዛፎች አጠገብ ተቀመጠ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።
ዘፍጥረት 13 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 13
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 13:8-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች