በባቢሎን ቤተ መንግሥት የሚገኙ መዛግብት ሁሉ ይመረመሩ ዘንድ ንጉሠ ነገሥት ዳርዮስ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ነገር ግን በባቢሎን ከተማ ሳይሆን በሜዶን ክፍለ ሀገር በተለይ “አሕምታ” ተብላ በምትጠራው ከተማ ውስጥ አንድ የብራና ጥቅል ተገኘ፤ በውስጡም የተጻፈበት ቃል እንዲህ የሚል ነበር፦ “ቂሮስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በመጀመሪያው ዓመት በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ የሚቃጠለውና ሌላውም ልዩ ልዩ መሥዋዕት ይቀርብበት ዘንድ እንደገና እንዲሠራ በመፍቀድ ትእዛዝ ሰጥቶአል፤ የቤተ መቅደሱም ርዝመት ኻያ ሰባት ሜትር፥ ስፋቱም ኻያ ሰባት ሜትር መሆን አለበት። ቅጽሮቹም ከድንጋይ በተሠሩት በሦስቱም ዙር ግንቦች አናት ላይ አንዳንድ ዙር ከእንጨት የተሠራ ድምድማት ይኑራቸው፤ ለዚህም ሁሉ ሥራ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ወጪ ሆኖ ይሰጥ። እንዲሁም ከዚህ በፊት ንጉሥ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ ማርኮ ያወጣቸው ከወርቅና ከብር የተሠሩትም ንዋያተ ቅድሳት ወደዚያው ተመልሰው በኢየሩሳሌም በሚሠራው ቤተ መቅደስ በተገቢ ቦታቸው ይቀመጡ።” ከዚህ በኋላ ዳርዮስ የሚከተለውን መልእክት አስተላለፈ፦ “የኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ገዢ ለሆንከው ለታተናይ፥ ለሸታርቦዝናይና በኤፍራጥስ ምዕራብ ለሚገኙ ተባባሪዎቻችሁ ሁሉ፦ ከቤተ መቅደሱ ራቁ፤ ሥራውን ከማደናቀፍ ተቈጠቡ፤ የይሁዳ ክፍለ ሀገር ገዢና የአይሁድ መሪዎች ቀድሞ በነበረበት ስፍራ ላይ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መልሰው ይሥሩ። በዚሁ አጋጣሚ ይልቁንም የቤተ መቅደሱን ሥራ እንድታግዙአቸው አዝዣችኋለሁ። ስለዚህም አስፈላጊው የማሠሪያ ገንዘብ ሁሉ ከኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ከተሰበሰበው የመንግሥት ግብር ሳይዘገይ ወጪ እየሆነ ይሰጣቸው፤ ሥራውም መሰናከል አይገባውም። ከዚህም ሁሉ ጋር በኢየሩሳሌም የሚገኙት ካህናት በሚነግሩአችሁ መሠረት በየዕለቱ በሰማይ ለሚኖረው አምላክ ለሚያቀርቡት መሥዋዕት የሚፈልጓቸውን ኰርማዎች፥ በጎችን ወይም ጠቦቶችን፥ እንዲሁም ለመባ የሚሆነውን ስንዴ፥ ጨው፥ የወይን ጠጅና የወይራ ዘይት ሁሉ ስጡአቸው። ይህም ሁሉ የሚሆንበት ምክንያት የሰማይ አምላክ በደስታ የሚቀበለውን መሥዋዕት ሁሉ በማቅረብ ለእኔና ለልጆቼ ሕይወት እንዲጸልዩልን ነው፤ ከዚህም ሌላ ማስታወቅ የምፈልገው ነገር ይህን መመሪያ የማይቀበልና የማይታዘዝ ማንም ሰው ቢኖር ከቤቱ የእንጨት ምሰሶዎች አንዱ ተነቅሎ በአንዱ ጫፍ በኩል እንዲሾል ከተደረገ በኋላ በሰውነቱ ላይ ይሰካበት፤ ቤቱም ፈራርሶ የጉድፍ መጣያ ይሁን። ይህን ትእዛዝ ባለመቀበል በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማፍረስ የሚሞክረውን ማንኛውንም ንጉሥ ወይም ሕዝብ የስሙ መጠሪያ ይሆን ዘንድ የመረጠ አምላክ ያስወግደው፤ ይህን ትእዛዝ ያስተላለፍኩ እኔ ዳርዮስ ስለ ሆንኩ በሙሉ መፈጸም አለበት።”
መጽሐፈ ዕዝራ 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ዕዝራ 6:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች