መጽሐፈ ዕዝራ 5:1-5

መጽሐፈ ዕዝራ 5:1-5 አማ05

በዚያን ጊዜ ሁለቱ ነቢያት፥ ሐጌና የዒዶ ልጅ ዘካርያስ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር ለሚኖሩ አይሁድ፥ ስለ ቤተ መቅደሱ ሥራ ጉዳይ በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው። የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኢዮጼዴቅ ልጅ ኢያሱም የነዚህን ነቢያት የትንቢት ቃል በሰሙ ጊዜ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ መሥራታቸውን እንደገና ቀጠሉ፤ ሁለቱ ነቢያትም ይረዱአቸው ነበር። በዚያን ጊዜ የኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ገዢ የነበረው ታተናይና ሽታርቦዝናይ እንዲሁም ተባባሪዎቻቸው የሆኑ ባለሥልጣኖች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፦ “ይህን ቤተ መቅደስ ለመሥራትና ቅጽሩንም ለማደስ ማን ፈቀደላችሁ?” ሲሉ ጠየቁአቸው። ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተባበሩአቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ለማወቅም ጠየቁ። ነገር ግን የአይሁድ መሪዎችን እግዚአብሔር ይጠብቃቸው ስለ ነበር ለፋርስ ባለ ሥልጣኖች ለዳርዮስ መልእክት ጽፈው መልስ እስከሚያገኙ ድረስ ሥራውን ከመቀጠል አልከለከሉአቸውም።