መጽሐፈ ዕዝራ 4:1-5

መጽሐፈ ዕዝራ 4:1-5 አማ05

የይሁዳና የብንያም ሕዝብ ጠላቶች የሆኑ ነዋሪዎች ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ሰሙ። ወደ ዘሩባቤልና ወደ ጐሣ መሪዎችም ቀርበው “ቤተ መቅደሱን ከእናንተ ጋር አብረን እንሥራ፤ ይህንኑ እናንተ የምታመልኩትን እግዚአብሔር እኛም እናመልከዋለን፤ የአሦር ንጉሠ ነገሥት አስራዶን ወደዚህ አገር ከላከንም ጊዜ ጀምሮ መሥዋዕት ስናቀርብለት ቈይተናል” አሉአቸው። ነገር ግን ዘሩባቤል፥ ኢያሱና የጐሣ መሪዎች ሁሉ እነዚህን ሰዎች፦ “ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ስለምንሠራው ቤተ መቅደስ የእናንተ ርዳታ አያስፈልገንም፤ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ቂሮስ ባዘዘን መሠረት እኛው ራሳችን እንሠራዋለን” ሲሉ መለሱላቸው። ከዚህም በኋላ የምድሪቱ ነዋሪዎች የሆኑት ሕዝቦች አይሁድን በማስፈራራትና ተስፋ ለማስቈረጥ በመሞከር ቤተ መቅደሱን እንዳይሠሩ ሊከለክሉአቸው ተነሣሡ። ለፋርስ መንግሥት ባለሥልጣኖች ጉቦ በመስጠትም በእነርሱ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርጉባቸው ሞከሩ፤ ከቂሮስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ዳርዮስ እስከ ተነሣበት ዘመን ድረስ ይህን ከማድረግ አልተቈጠቡም ነበር።