እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ከአንድ እናት የሚወለዱ ሁለት እኅትማማች ነበሩ፤ እነርሱም በወጣትነታቸው ወራት በግብጽ ሲኖሩ ክብርናቸውን አጥተው በመዋረድ አመንዝሮች ሆኑ። ከእነርሱም ታላቂቱ ኦሆላ ትባል ነበር፤ እርስዋም ሰማርያ ነች፤ ታናሽቱ ደግሞ ኦሆሊባ ትባል ነበር እርስዋም ኢየሩሳሌም ነች፤ እኔ ሁለቱንም አግብቼ ልጆች ወለዱልኝ። ኦሆላ እኔ ካገባኋት በኋላ እንኳ አመንዝራነትዋን ቀጠለች፤ በአሦራውያን ወዳጆችዋም ፍቅር ተቃጠለች። እነርሱም ሐምራዊ የለበሱ ታላላቅ መሳፍንት፥ ከፍተኛ ማዕርግ ያላቸው መኰንኖች ነበሩ፤ ሁሉም ወጣትነት ያላቸውና መልከ ቀና የሆኑ ፈረሰኞች ነበሩ። እርስዋም ለአሦራውያን ባለ ሥልጣኖች ሁሉ መጠቀሚያ አመንዝራ ነበረች፤ ፍትወትዋም የአሦራውያንን ጣዖቶች በማምለክ ራስዋን እንድታረክስ አደረጋት። ክብርናዋን ባጣችበት በግብጽ የጀመረችውን አመንዝራነት ቀጥላለች፤ ከልጃገረድነትዋ ጊዜ ጀምሮ ወንዶች ሁሉ እርስዋን እንደ አመንዝራ በመቊጠር ከእርስዋ ጋር ያመነዝራሉ። ስለዚህ እጅግ ለምትፈልጋቸው ለአሦራውያን ወዳጆችዋ አሳልፌ ሰጠኋት፤ እነርሱም ልብስዋን ገፈው እርቃንዋን አስቀሩአት፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችዋን በምርኮ ያዙ፤ እርስዋንም በሰይፍ ገደሉአት፤ ፍርድም በእርስዋ ላይ ተግባራዊ ሆነ፤ ሴቶች ሁሉ ስለ ገጠማት መጥፎ ዕድል አሉባልታ ማሰማት ጀመሩ። “እኅትዋ ኦሆሊባ ይህንንም ካየች በኋላ ባሰባት እንጂ አልታረመችም፤ እንዲያውም ከኦሆላ የበለጠ አመንዝራ ሆነች። እርስዋም በበኩልዋ ታላላቅ የአሦራውያን መሳፍንትንና የጦር መኰንኖችን፥ ደማቅ ልብስ የሚለብሱ ወታደሮችንና መልከቀና የሆኑ ወጣትነት ያላቸውን ፈረሰኞች በማፍቀር በፍትወት የተቃጠለች ሆነች። ይህችም ሁለተኛይቱ ረከሰች፤ ሁለቱም በአንድ ዐይነት መንገድ ተጓዙ። “አመንዝራነትዋም እየባሰ ሄደ፤ በወገቦቻቸው ዙሪያ የሚያማምሩ ቀለበቶችን ታጥቀው፥ በራሶቻቸውም ላይ ጌጠኛ ጥምጥም ጠምጥመው፥ በደማቅ ሐምራዊ ቀለም በግድግዳ ላይ የተቀረጹትን ከፍተኞች የሆኑት ባለሥልጣኖችን ምስሎች አይታ ተማረከች። ልክ እነርሱን ስታይ በፍትወት ተቃጥላ እነርሱ ወደሚኖሩባት ወደ ባቢሎን መልእክተኞችን ላከች፤ ባቢሎናውያንም ከእርስዋ ጋር ለማመንዘር መጡ፤ ብዙ ጊዜ ስላረከሱአት በመጨረሻ ሁሉንም በመጸየፍ ጠላቻቸው። እርቃንዋን ወደ አደባባይ በመውጣት አመንዝራነትዋ በሰው ሁሉ ዘንድ እንዲጋለጥ አደረገች፤ እኔም እኅትዋን የተጸየፍኩትን ያኽል እርስዋንም ተጸየፍኳት። እርስዋም በልጃገረድነትዋ ወራት በግብጽ አመንዝራ ሆና ሳለ ስታደርግ የነበረውን ሁሉ በመፈጸም አመንዝራነትዋን አበዛች። ብልቶቻቸው እንደ አህያ፥ ዘራቸውም እንደ አለሌ ፈረስ ሆኖ በፍትወት በሚቃጠሉ ወንዶች ተማረከች። ኦሆሊባ ሆይ! በልጃገረድነትሽ ወራት ወንዶች በጡቶችሽ እየተጫወቱ ክብረ ንጽሕናሽን ባጣሽ ጊዜ ትፈጽሚው የነበረውን ርኲሰት ደግመሽ መፈጸም ትፈልጊያለሽ። “አሁንም ኦሆሊባ ሆይ! እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምልሽ ይህ ነው፤ እነዚያን ወዳጆችሽን ተጸይፈሻቸዋል፤ ነገር ግን እነርሱ በአንቺ እንዲነሡ አደርጋለሁ፤ እንዲከቡሽም ወደዚህ አመጣቸዋለሁ። ባቢሎናውያንንና ከለዳውያንን ሁሉ አመጣለሁ፤ የፈቆድን፥ የሾዐንና የቆዐንን ወንዶች እንዲሁም አሦራውያንን ሁሉ አመጣለሁ፤ ወጣትነት ያላቸው፥ መልከ ቀና የሆኑ መሳፍንትና የጦር መኰንኖች፥ ታላላቅ ባለሥልጣኖችና ከፍተኛ ማዕርግ ያላቸው እነዚህ ሁሉ በፈረስ ተቀምጠው ይመጣሉ። እነርሱም በብዙ ሠረገላና ስንቅ በተጫኑ ጋሪዎች የተጠናከረ ታላቅ ሠራዊት መርተው በማምጣት በሁሉም አቅጣጫ አደጋ ይጥሉብሻል፤ በጋሻና በራስ ቊር እየተከላከሉ ይከቡሻል፤ እኔም ለእነርሱ ፍርድ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ እነርሱም በራሳቸው ሕግ መሠረት ይቀጡሻል። እኔ በአንቺ ስለ ተቈጣሁ፤ እነርሱም በቊጣቸው በአንቺ ላይ የፈለጉትን እንዲያደርጉ እፈቅድላቸዋለሁ፤ አፍንጫሽንና ጆሮዎችሽን ይቈርጣሉ፤ ከአንችም የቀሩትን በሰይፍ ይገደላሉ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን ከአንቺ ነጥቀው ይወስዳሉ፤ ከአንቺም የቀሩትን በእሳት ያቃጥሉአቸዋል። ልብሶችሽን ሁሉ ይገፉሻል፤ ጌጣጌጦችሽንም ሁሉ ይወስዳሉ። የዝሙት ሥራሽንና ገና በግብጽ ሳለሽ ጀምሮ የምትፈጽሚያቸውን አሳፋሪ ድርጊቶች ሁሉ እንድትተይ አደርጋለሁ፤ ዳግመኛም ወደ ጣዖቶች አትመለከቺም፤ ስለ ግብጽም አታስቢም።” ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “በጥላቻ ለምትጸየፊያቸው ሕዝቦች አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ አንቺን ከመጥላታቸው የተነሣ የደከምሽበትን ሁሉ ይወስዱብሻል፤ እርቃንሽንም አስቀርተው እንደ አመንዝራ ሴት ኀፍረተ ሥጋሽ እንዲጋለጥ ያደርጋሉ፤ የተቃጠለ ፍትወትሽና ዘማዊነትሽ፥ ይህ ሁሉ እንዲደርስብሽ አድርጎአል፤ ለሕዝቦች ሁሉ የፍትወት መጠቀሚያ ዘማዊት ሆነሽ በጣዖቶቻቸው ራስሽን አረከስሽ። የእኅትሽን አካሄድ ስለ ተከተልሽ እርስዋ የጠጣችውን የቅጣት ጽዋ እንድትጠጪ አደርግሻለሁ።” ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነሆ ከእኅትሽ ጽዋ ትጠጪአለሽ፤ እርሱም ትልቅና ጥልቀት ያለው ነው፤ ሰው ሁሉ መቀለጃና ማፌዣ ያደርግሻል፤ ጽዋውም ብዙ የሚይዝ ነው። አንቺ በስካርና በሐዘን የተሞላሽ ትሆኚአለሽ፤ የእኅትሽ የሰማርያንም የጥፋትና የውድመት ጽዋ ትጠጪአለሽ። ምንም ሳታስቀሪ ጨልጠሽ ትጠጪዋለሽ፤ ጽዋውንም ሰባብረሽ በስባሪው በሐዘን ጡቶችሽን ትቈራርጪአለሽ። እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” አሁንም ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “ስለ ረሳሽኝና ጀርባሽን ስላዞርሽብኝ፥ ስለ ሴሰኛነትሽና ስለ አመንዝራነትሽም መከራ ትቀበዪአለሽ።” እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! በኦሆላና በኦሆሊባ ላይ ፍርድ ለመስጠት ተዘጋጅተሃልን? ያደረጉትን አጸያፊ ነገር ግለጥላቸው፤ ሁለቱም አመንዝሮችና ነፍሰ ገዳዮች ናቸው፤ ያመነዘሩት ከጣዖቶች ጋር ሲሆን፥ የገደሉአቸውም ለእኔ የወለዱአቸውን ልጆች ነው፤ ወንዶች ልጆቼን ለጣዖቶቻቸው ሠውተዋል። እነርሱ የፈጸሙት በደል ይህ ብቻ አይደለም፤ ቤተ መቅደሴንም በዚያን ጊዜ አርክሰዋል፤ ሰንበቴንም ሽረዋል። ለጣዖቶች መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ ልጆቼን በገደሉበት ዕለት ወደ ቤተ መቅደሴ መጥተው አረከሱት፤ እነሆ በቤቴ ያደረጉት ይህ ነው።
ትንቢተ ሕዝቅኤል 23 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ሕዝቅኤል 23:1-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች