የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 16:1-14

ትንቢተ ሕዝቅኤል 16:1-14 አማ05

እግዚአብሔርም እንደገና እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ኢየሩሳሌም ያደረገችው ነገር ምን ያኽል አጸያፊ እንደ ሆነ አስታውቃት፤ ልዑል እግዚአብሔር ስለ እርስዋ የሚለውንም እንዲህ ብለህ ንገራት፦ “የተወለድሽው በከነዓን ምድር ነበር፤ አባትሽ አሞራዊ ሲሆን እናትሽም ሒታዊ ነበረች፤ በተወለድሽ ጊዜ እትብትሽን አልተቈረጠም፤ ንጹሕ ትሆኚ ዘንድ በውሃ አልታጠብሽም፥ ወይም በጨው ታሽተሽ በጨርቅ አልተጠቀለልሽም። ከነዚህ ነገሮች አንዱን እንኳ ለማድረግ ለአንቺ ርኅራኄ ያለው ማንም አልነበረም፤ ስትወለጂ የተጠላሽ ስለ ነበርሽ በሜዳ ላይ ተጣልሽ። “እኔም በዚያ ሳልፍ በገዛ ደምሽ ተነክረሽ ስትንፈራገጪ አገኘሁሽ፤ በደም ተሸፍነሽ ልትሞቺ ነበረ፤ በሕይወት እንድትኖሪ አደረግሁሽ። ምቾት እንዳለው ተክል እንድታድጊ አደረግሁ፤ ቁመትና ጠንካራ ሰውነት በመጨመር አድገሽ የተዋብሽ ወጣት ሆንሽ፤ ጡትሽ አጐጠጐጠ፤ ጠጒርሽ ረዘመ፤ ነገር ግን እርቃንሽን ነበርሽ። “እንደገናም በአጠገብሽ ሳልፍ ጊዜሽ የፍቅር ዕድሜ ነበር፤ የተራቈተውን ሰውነትሽንም በመጐናጸፊያዬ ሸፍኜ ቃል ገባሁልሽ፤ ከአንቺም ጋር እንደ ጋብቻ ያለ ቃል ኪዳን ገብቼ የእኔ የግሌ አደረግሁሽ፤” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው። “ከዚያም በኋላ መላ አከላትሽንና በደም የተበከለ ሰውነትሽን አጠብኩ፤ የወይራ ዘይትም ቀባሁሽ፤ ጥበብ ቀሚስ አለበስኩሽ፤ ከምርጥ ቆዳ የተሠራ ጫማ አደረግሁልሽ፤ ሐር ሻሽ በራስሽ ላይ አሰርኩልሽ፤ ውድ የሆነ ካባ ደረብኩልሽ። በጌጥ አስጌጥኩሽ፤ የእጅ አንባርና የአንገት ድሪ አደረግሁልሽ። ለአፍንጫሽ ቀለበት፥ ለጆሮሽ ጒትቻ፥ እንዲሁም በራስሽ ላይ የምትደፊው ውብ የሆነ አክሊል ሰጠሁሽ። ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ብዙ ጌጣጌጦች ነበሩሽ፤ ከልዩ ልዩ ሐር የተሠሩና በጥልፍ ጌጥ የተዋቡ ውድ ልብሶች ነበሩሽ፤ ምርጥ ከሆነ ዱቄት የተጋገረ ዳቦ፥ ማርና የወይራ ዘይት ትመገቢ ነበር፤ ውበትሽ እጅግ እየጨመረ ስለ ሄደ ንግሥት ለመሆን በቃሽ። ግርማ ሞገሴን በአንቺ ላይ አሳርፌ የተዋብሽ ስላደረግሁሽ እንከን ከሌለበት ቊንጅናሽ የተነሣ በሁሉ አገር ታወቅሽ።” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።