የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለኢየሩሳሌም አስጸያፊ ተግባሯን ፊት ለፊት ንገራት፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲህ ይላታል፤ ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፤ አባትሽ አሞራዊ፣ እናትሽም ኬጢያዊት ነበሩ። በተወለድሽበት ቀን ዕትብትሽ አልተቈረጠም፤ ንጹሕ እንድትሆኚ በውሃ አልታጠብሽም፤ በጨው አልታሸሽም፤ በጨርቅም አልተጠቀለልሽም። በርኅራኄ ዐይን ተመልክቶሽ ወይም ዐዝኖልሽ ከእነዚህ አንዱን እንኳ ያደረገልሽ ሰው አልነበረም፤ ይልቁንም በተወለድሽበት ቀን ተንቀሽ ስለ ነበር ሜዳ ላይ ተጣልሽ። “ ‘እኔም በዚያ ሳልፍ፣ በደምሽ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ስትንፈራገጪ አየሁሽ፤ በደምሽም ውስጥ ተኝተሽ ሳለሽ፣ “በሕይወት ኑሪ!” አልሁሽ። ሜዳ ላይ እንዳለ ቡቃያ አሳደግሁሽ፤ አንቺም አደግሽ፤ ብርቅ ዕንቍ ሆንሽ። ጡቶችሽ አጐጠጐጡ፤ ጠጕርሽም አደገ፤ ነገር ግን ከእናትሽ ማሕፀን እንደ ወጣሽ ዕርቃንሽን ነበርሽ። “ ‘ዳግመኛም በአጠገብሽ በማልፍበት ጊዜ ወደ አንቺ ተመለከትሁ፤ ለመፈቀርም እንደ ደረስሽ ባየሁ ጊዜ፣ የመጐናጸፊያዬን ዘርፍ በላይሽ ዘርግቼ ዕርቃንሽን ሸፈንሁ። ማልሁልሽ፤ ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ተጋባሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺም የእኔ ሆንሽ። “ ‘በውሃ ዐጥቤ ከደም አጠራሁሽ፤ ዘይትም ቀባሁሽ። ወርቀ ዘቦ አለበስሁሽ፤ ምርጥ ቈዳ ጫማም አደረግሁልሽ፤ ያማረ በፍታ አለበስሁሽ ውድ መደረቢያም አጐናጸፍሁሽ። በጌጣጌጥ አንቈጠቈጥሁሽ፤ በእጅሽ አንባር፣ በዐንገትሽም ድሪ አጠለቅሁልሽ፤ በአፍንጫሽ ቀለበት፣ በጆሮሽ ጕትቻ፣ በራስሽም ላይ ውብ አክሊል አደረግሁልሽ፤ በወርቅና በብር አጌጥሽ፤ ልብስሽም ያማረ በፍታ፣ ሐርና ወርቀ ዘቦ ነበር፤ ምግብሽም የላመ ዱቄት፣ ማርና የወይራ ዘይት ነበር። እጅግ ውብ ሆንሽ፤ ንግሥት ለመሆንም በቃሽ። እኔ ከሰጠሁሽ ሞገስ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም በመሆኑ ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ገነነ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ሕዝቅኤል 16 ያንብቡ
ያዳምጡ ሕዝቅኤል 16
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሕዝቅኤል 16:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos