የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሕዝቅኤል 16:1-14

ሕዝቅኤል 16:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለኢየሩሳሌም አስጸያፊ ተግባሯን ፊት ለፊት ንገራት፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲህ ይላታል፤ ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፤ አባትሽ አሞራዊ፣ እናትሽም ኬጢያዊት ነበሩ። በተወለድሽበት ቀን ዕትብትሽ አልተቈረጠም፤ ንጹሕ እንድትሆኚ በውሃ አልታጠብሽም፤ በጨው አልታሸሽም፤ በጨርቅም አልተጠቀለልሽም። በርኅራኄ ዐይን ተመልክቶሽ ወይም ዐዝኖልሽ ከእነዚህ አንዱን እንኳ ያደረገልሽ ሰው አልነበረም፤ ይልቁንም በተወለድሽበት ቀን ተንቀሽ ስለ ነበር ሜዳ ላይ ተጣልሽ። “ ‘እኔም በዚያ ሳልፍ፣ በደምሽ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ስትንፈራገጪ አየሁሽ፤ በደምሽም ውስጥ ተኝተሽ ሳለሽ፣ “በሕይወት ኑሪ!” አልሁሽ። ሜዳ ላይ እንዳለ ቡቃያ አሳደግሁሽ፤ አንቺም አደግሽ፤ ብርቅ ዕንቍ ሆንሽ። ጡቶችሽ አጐጠጐጡ፤ ጠጕርሽም አደገ፤ ነገር ግን ከእናትሽ ማሕፀን እንደ ወጣሽ ዕርቃንሽን ነበርሽ። “ ‘ዳግመኛም በአጠገብሽ በማልፍበት ጊዜ ወደ አንቺ ተመለከትሁ፤ ለመፈቀርም እንደ ደረስሽ ባየሁ ጊዜ፣ የመጐናጸፊያዬን ዘርፍ በላይሽ ዘርግቼ ዕርቃንሽን ሸፈንሁ። ማልሁልሽ፤ ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ተጋባሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺም የእኔ ሆንሽ። “ ‘በውሃ ዐጥቤ ከደም አጠራሁሽ፤ ዘይትም ቀባሁሽ። ወርቀ ዘቦ አለበስሁሽ፤ ምርጥ ቈዳ ጫማም አደረግሁልሽ፤ ያማረ በፍታ አለበስሁሽ ውድ መደረቢያም አጐናጸፍሁሽ። በጌጣጌጥ አንቈጠቈጥሁሽ፤ በእጅሽ አንባር፣ በዐንገትሽም ድሪ አጠለቅሁልሽ፤ በአፍንጫሽ ቀለበት፣ በጆሮሽ ጕትቻ፣ በራስሽም ላይ ውብ አክሊል አደረግሁልሽ፤ በወርቅና በብር አጌጥሽ፤ ልብስሽም ያማረ በፍታ፣ ሐርና ወርቀ ዘቦ ነበር፤ ምግብሽም የላመ ዱቄት፣ ማርና የወይራ ዘይት ነበር። እጅግ ውብ ሆንሽ፤ ንግሥት ለመሆንም በቃሽ። እኔ ከሰጠሁሽ ሞገስ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም በመሆኑ ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ገነነ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 16:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል ወደ እኔ እን​ዲህ ሲል መጣ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ለኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ኀጢ​አ​ት​ዋን አስ​ታ​ው​ቃት፤ እን​ዲ​ህም በላት፦ ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም እን​ዲህ ይላል፦ ዘር​ሽና ትው​ል​ድሽ ከከ​ነ​ዓን ምድር ነው፤ አባ​ትሽ አሞ​ራዊ ነበረ፤ እና​ት​ሽም ኬጢ​ያ​ዊት ነበ​ረች። በተ​ወ​ለ​ድሽ ጊዜ በዚ​ያው ቀን እት​ብ​ትሽ አል​ታ​ተ​በም፤ ንጹ​ሕም ትሆኚ ዘንድ በውኃ አል​ታ​ጠ​ብ​ሽም፤ በጨ​ውም አል​ተ​ወ​ለ​ወ​ል​ሽም፤ በጨ​ር​ቅም አል​ተ​ጠ​ቀ​ለ​ል​ሽም፤ በጭ​ንም አል​ታ​ቀ​ፍ​ሽም። በተ​ወ​ለ​ድ​ሽ​በት ቀን ከሰ​ው​ነ​ትሽ ጕስ​ቍ​ልና የተ​ነሣ በሜዳ ላይ ተጣ​ልሽ እንጂ፥ ከዚህ አን​ዳች ይደ​ረ​ግ​ልሽ ዘንድ ዐይኔ አል​ራ​ራ​ል​ሽም፤ ማንም አላ​ዘ​ነ​ል​ሽም። “በአ​ን​ቺም ዘንድ ባለ​ፍሁ ጊዜ፤ በደ​ም​ሽም ተለ​ው​ሰሽ በአ​የ​ሁሽ ጊዜ፦ ከደ​ምሽ ዳኝ አል​ሁሽ፤ በእ​ርሻ ላይ እንደ አለ ቡቃያ አበ​ዛ​ሁሽ፤ አን​ቺም አደ​ግሽ፤ ታላ​ቅም ሆንሽ፤ በእ​ጅ​ጉም አጌ​ጥሽ፤ ከከ​ተማ ወደ ከተማ ገባሽ፤ ጡቶ​ች​ሽም አጐ​ጠ​ጐጡ፤ ጠጕ​ር​ሽም አደገ፤ ነገር ግን ዕር​ቃ​ን​ሽን ሆንሽ፤ ተራ​ቍ​ተ​ሽም ነበ​ርሽ። በአ​ንቺ ዘንድ በአ​ለ​ፍ​ሁና በአ​የ​ሁሽ ጊዜ፥ እነሆ ጊዜሽ እንደ ደረሰ፥ በአ​ን​ቺም የሚ​ያ​ድሩ ሰዎች ጊዜ እንደ ደረሰ አየሁ። እጆ​ችን በላ​ይሽ ዘረ​ጋሁ፤ ኀፍ​ረተ ሥጋ​ሽ​ንም ከደ​ንሁ፤ ማል​ሁ​ል​ሽም፤ ከአ​ን​ቺም ጋራ ቃል ኪዳን ገባሁ፥” ይላል ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፤ አን​ቺም ለእኔ ሆንሽ። በው​ኃም አጠ​ብ​ሁሽ፤ ከደ​ም​ሽም አጠ​ራ​ሁሽ፤ በዘ​ይ​ትም ቀባ​ሁሽ። ወርቀ ዘቦም አለ​በ​ስ​ሁሽ፤ ጥቁር ጫማም አደ​ረ​ግ​ሁ​ልሽ፤ በጥሩ በፍታ አስ​ታ​ጠ​ቅ​ሁሽ፤ በሐ​ርም ከደ​ን​ሁሽ። በጌ​ጥም አስ​ጌ​ጥ​ሁሽ፤ በእ​ጅ​ሽም ላይ አን​ባር፥ በአ​ን​ገ​ት​ሽም ላይ ድሪ አደ​ረ​ግ​ሁ​ልሽ። በአ​ፍ​ን​ጫ​ሽም ቀለ​በት፥ በጆ​ሮ​ሽም ጉትቻ፥ በራ​ስ​ሽም ላይ የክ​ብር አክ​ሊል አደ​ረ​ግሁ። በወ​ር​ቅና በብር አጌ​ጥሽ፤ ልብ​ስ​ሽም ጥሩ በፍ​ታና ሐር፥ ወርቀ ዘቦም ነበረ፤ አን​ቺም መል​ካ​ምን ዱቄ​ትና ማርን፥ ዘይ​ት​ንም በላሽ፤ ወፈ​ርሽ፤ እጅ​ግም ውብ ሆንሽ፤ ለመ​ን​ግ​ሥ​ትም የተ​ዘ​ጋ​ጀሽ አደ​ረ​ግ​ሁሽ። ባንቺ ላይ ከአ​ኖ​ር​ኋት ከክ​ብሬ የተ​ነሣ ውበ​ትሽ ፍጹም ነበ​ረና ስምሽ በአ​ሕ​ዛብ መካ​ከል ተሰማ፥ ይላል ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር።

ሕዝቅኤል 16:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለኢየሩሳሌም ርኵሰትዋን አስታውቃት፥ እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይላል፦ ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፥ አባትሽ አሞራዊ ነበረ እናትሽም ኬጢያዊት ነበረች። በተወለድሽ ጊዜ በዚያው ቀን እትብትሽ አልተቈረጠም ንጹሕም ትሆኚ ዘንድ በውኃ አልታጠብሽም፥ በጨውም አልተቀባሽም በጨርቅም አልተጠቀለልሽም። በተወለድሽበት ቀን ከሰውነትሽ ጕስቁልና የተነሣ በሜዳ ላይ ተጣልሽ እንጂ ከዚህ አንዳች ይደረግልሽ ዘንድ ዓይን አልራራልሽም፥ ማንም አላዘነልሽም። በአንቺም ዘንድ ባለፍሁ ጊዜ በደምሽም ውስጥ ተለውሰሽ ባየሁሽ ጊዜ፦ በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ፥ አዎን፦ በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ። በእርሻ ላይ እንዳለ ቡቃያ አበዛሁሽ፥ አንቺም አደግሽ ታላቅም ሆንሽ፥ በእጅጉም አጌጥሽ፥ ጡቶችሽም አጐጠጐጡ ጠጕርሽም አደገ፥ ነገር ግን ዕርቃንሽን ሆንሽ፥ ተራቍተሽም ነበርሽ። በአንቺ ዘንድ ባለፍሁና ባየሁሽ ጊዜ፥ እነሆ፥ ጊዜሽ የፍቅር ጊዜ ነበረ፥ እኔም መጐናጸፊያዬን በላይሽ ዘረጋሁ ኅፍረተ ሥጋሽንም ከደንሁ፥ ማልሁልሽም ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ አንቺም ለእኔ ሆንሽ። በውኃም አጠብሁሽ ከደምሽም አጠራሁሽ በዘይትም ቀባሁሽ። ወርቀ ዘቦም አለበስሁሽ በአቆስጣ ቁርበትም ጫማ አደረግሁልሽ፥ በጥሩ በፍታ አስታጠቅሁሽ በሐርም ከደንሁሽ። በጌጥም አስጌጥሁሽ በእጅሽም ላይ አንባር በአንገትሽም ላይ ድሪ አደረግሁልሽ። በአፍንጫሽም ቀለበት በጆሮሽም ጕትቻ በራስሽም ላይ የክብር አክሊል አደረግሁ። በወርቅና በብር አጌጥሽ፥ ልብስሽም ጥሩ በፍታና ሐር ወርቀ ዘቦም ነበረ፥ አንቺም መልካም ዱቄትና ማርን ዘይትንም በላሽ፥ እጅግ በጣም ውብ ሆንሽ ለመንግሥትም ደረስሽ። ባንቺ ላይ ካኖርኋት ከክብሬ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ወጣ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሕዝቅኤል 16:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔርም እንደገና እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ኢየሩሳሌም ያደረገችው ነገር ምን ያኽል አጸያፊ እንደ ሆነ አስታውቃት፤ ልዑል እግዚአብሔር ስለ እርስዋ የሚለውንም እንዲህ ብለህ ንገራት፦ “የተወለድሽው በከነዓን ምድር ነበር፤ አባትሽ አሞራዊ ሲሆን እናትሽም ሒታዊ ነበረች፤ በተወለድሽ ጊዜ እትብትሽን አልተቈረጠም፤ ንጹሕ ትሆኚ ዘንድ በውሃ አልታጠብሽም፥ ወይም በጨው ታሽተሽ በጨርቅ አልተጠቀለልሽም። ከነዚህ ነገሮች አንዱን እንኳ ለማድረግ ለአንቺ ርኅራኄ ያለው ማንም አልነበረም፤ ስትወለጂ የተጠላሽ ስለ ነበርሽ በሜዳ ላይ ተጣልሽ። “እኔም በዚያ ሳልፍ በገዛ ደምሽ ተነክረሽ ስትንፈራገጪ አገኘሁሽ፤ በደም ተሸፍነሽ ልትሞቺ ነበረ፤ በሕይወት እንድትኖሪ አደረግሁሽ። ምቾት እንዳለው ተክል እንድታድጊ አደረግሁ፤ ቁመትና ጠንካራ ሰውነት በመጨመር አድገሽ የተዋብሽ ወጣት ሆንሽ፤ ጡትሽ አጐጠጐጠ፤ ጠጒርሽ ረዘመ፤ ነገር ግን እርቃንሽን ነበርሽ። “እንደገናም በአጠገብሽ ሳልፍ ጊዜሽ የፍቅር ዕድሜ ነበር፤ የተራቈተውን ሰውነትሽንም በመጐናጸፊያዬ ሸፍኜ ቃል ገባሁልሽ፤ ከአንቺም ጋር እንደ ጋብቻ ያለ ቃል ኪዳን ገብቼ የእኔ የግሌ አደረግሁሽ፤” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው። “ከዚያም በኋላ መላ አከላትሽንና በደም የተበከለ ሰውነትሽን አጠብኩ፤ የወይራ ዘይትም ቀባሁሽ፤ ጥበብ ቀሚስ አለበስኩሽ፤ ከምርጥ ቆዳ የተሠራ ጫማ አደረግሁልሽ፤ ሐር ሻሽ በራስሽ ላይ አሰርኩልሽ፤ ውድ የሆነ ካባ ደረብኩልሽ። በጌጥ አስጌጥኩሽ፤ የእጅ አንባርና የአንገት ድሪ አደረግሁልሽ። ለአፍንጫሽ ቀለበት፥ ለጆሮሽ ጒትቻ፥ እንዲሁም በራስሽ ላይ የምትደፊው ውብ የሆነ አክሊል ሰጠሁሽ። ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ብዙ ጌጣጌጦች ነበሩሽ፤ ከልዩ ልዩ ሐር የተሠሩና በጥልፍ ጌጥ የተዋቡ ውድ ልብሶች ነበሩሽ፤ ምርጥ ከሆነ ዱቄት የተጋገረ ዳቦ፥ ማርና የወይራ ዘይት ትመገቢ ነበር፤ ውበትሽ እጅግ እየጨመረ ስለ ሄደ ንግሥት ለመሆን በቃሽ። ግርማ ሞገሴን በአንቺ ላይ አሳርፌ የተዋብሽ ስላደረግሁሽ እንከን ከሌለበት ቊንጅናሽ የተነሣ በሁሉ አገር ታወቅሽ።” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።

ሕዝቅኤል 16:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለኢየሩሳሌም ርኩሰትዋን አስታውቃት፥ እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲህ ይላታል፦ መሠረትሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፥ አባትሽ አሞራዊ ነበረ፥ እናትሽም ኬጢያዊት ነበረች። ስትወለጂ፥ በተወለድሽበት በዚያው ቀን እትብትሽ አልተቆረጠም ነበር፥ ንጹሕም እንድትሆኚ በውኃ አልታጠብሽም፥ በጨው አልታሸሽም፥ በጨርቅም አልተጠቀለልሽም። አዝኖልሽ ከእነዚህ ነገሮች አንዱን እንኳ ሊያደርግልሽ አንድም ዐይን አልራራልሽም፥ ነገር ግን በተወለድሽበት ቀን ሰውነትሽ የተጠላ ስለ ነበር በሜዳ ላይ ተጣልሽ። በአንቺም በኩል አለፍሁ፥ በደምሽም ውስጥ ስትንፈራገጪ አየሁሽ። በደምሽ እንዳለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ፥ አዎን በደምሽ ውስጥ እያለሽ በሕይወት ኑሪ አልሁሽ። በሜዳ ላይ እንዳለ ቡቃያ አበዛሁሽ፥ አንቺም አደግሽ ታላቅም ሆንሽ፥ በጌጦች አጌጥሽ፥ ጡቶችሽ አጐጠጐጡ፥ ጠጉርሽም አደገ፥ ሆኖም ዕርቃንሽንና ራቁትሽን ነበርሽ። በአንቺ በኩል አለፍሁ፥ አየሁሽም፥ እነሆ ጊዜሽ የፍቅር ጊዜ ነበር፥ እኔም መጐናጸፊያዬን በላይሽ ላይ ዘረጋሁና ዕርቃንሽን ሸፈንሁ፥ ማልሁልሽም ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ አንቺም የእኔ ሆንሽ። በውኃ አጠብሁሽ፥ ደምሽን ከላይሽ ላይ አጠራሁ፥ በዘይትም ቀባሁሽ። ወርቀ ዘቦም አለበስሁሽ፥ ከጥሩ ቆዳ የተሠራ ጫማ አደረግሁልሽ፥ በጥሩ በፍታ አስታጠቅሁሽ፥ ውድ መደረቢያም ደረብሁልሽ። በጌጥ አስጌጥሁሽ፥ በእጅሽ ላይ አንባር በአንገትሽም ላይ ሐብል አደረግሁልሽ። በአፍንጫሽ ቀለበት፥ በጆሮሽ ጉትቻ፥ በራስሽም ላይ ውብ አክሊል አደረግሁ። በወርቅና በብር አጌጥሽ፥ ልብስሽም ጥሩ በፍታ፥ ሐርና ወርቀዘቦ ነበር፥ የላመ ዱቄት፥ ማርና ዘይትም በላሽ፥ እጅግ በጣም ውብ ሆንሽ፥ ለንግሥትነትም በቃሽ። በአንቺ ላይ ካኖርኋት ከውበቴ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም ነበረና ስምሽ በሕዝቦች መካከል ወጣ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።