እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን “እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር መርታችሁ እንድታወጡ እኔ ያዘዝኳችሁ መሆኔን ለእስራኤላውያንና ለግብጽ ንጉሥ ንገሩ” ብሎ አዘዛቸው። የያዕቆብ በኲር ልጅ ሮቤል፥ ሐኖክ፥ ፋሉ፥ ሔጽሮንና ካርሚ የሚባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህም በየስማቸው የሮቤል ነገድ አባቶች ናቸው። ስምዖን ከከነዓናዊት ሴት የተወለደውን ሻኡልን ጨምሮ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ ያኪንና፥ ጾሓር የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህም በየስማቸው የስምዖን ነገድ አባቶች ናቸው። ሌዊ ጌርሾን፥ ቀዓትና መራሪ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህም በየስማቸው የሌዊ ነገድ አባቶች ናቸው፤ ሌዊ በሕይወት የኖረበት ዘመን 137 ዓመት ነበር። ጌርሾን፥ ሊብኒና ሺምዒ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ብዙ ዘሮች ነበሩአቸው። ቀዓት፥ ዓምራም፥ ይጽሐር፥ ኬብሮንና ዑዚኤል የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ቀዓት በሕይወት የኖረበት ዘመን 133 ዓመት ነው። መራሪ ማሕሊና ሙሺ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህና ዘሮቻቸው ሁሉ የሌዊ ወገኖች ናቸው። ዓምራም ዮኬቤድ የተባለችውን የአባቱን እኅት አገባ፤ እርስዋም አሮንንና ሙሴን ወለደችለት። ዓምራም በሕይወት የኖረበት ዘመን 137 ዓመት ነው። ይጽሐር ቆሬ፥ ኔፌግና ዚክሪ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ዑዚኤልም ሚሻኤል፥ ኤልጻፋንና ሲትሪ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት። አሮን የነአሶን እኅት የሆነችውን የዓሚናዳብን ልጅ ኤሊሼባን አገባ፤ እርስዋም ናዳብ፥ አቢሁ፥ አልዓዛርና ኢታማር የተባሉትን ወንዶች ልጆች ወለደችለት። ቆሬ አሲር፥ ኤልቃናና አቢያሳፍ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህም ለቆሬ ዘሮች ሁሉ የነገድ አባቶች ነበሩ። የአሮን ልጅ አልዓዛር የፑቲኤልን ልጅ አገባ፤ እርስዋም ፊኒሐስን ወለደችለት፤ እነዚህ ሁሉ የሌዊ የነገድ አባቶችና አለቆች ነበሩ። ከነዚህ መካከል እግዚአብሔር ሙሴና አሮን “የእስራኤልን ሕዝብ በየነገዳቸው ከግብጽ ምድር መርታችሁ አውጡ” ብሎ ያዘዛቸው ነው። “የእስራኤልን ሕዝብ ልቀቅ” ብለው ከግብጽ ንጉሥ ጋር የተነጋገሩ እነርሱ ናቸው። እግዚአብሔር ሙሴን በግብጽ ምድር በተናገረው ጊዜ፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እኔ የምነግርህን ሁሉ ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር” አለው። ሙሴ ግን “እኔ ኰልታፋ ነኝ፤ ታዲያ፥ ንጉሡ እንዴት ሊሰማኝ ይችላል?” ሲል መለሰ።
ኦሪት ዘጸአት 6 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 6:13-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos