ኦሪት ዘጸአት 6
6
1እግዚአብሔርም ሙሴን “በንጉሡ በፈርዖን ላይ የማደርገውን አሁን ታያለህ፤ በኀይሌ ተገዶ ሕዝቤን ይለቃል፤ በኀያል ክንዴም ተሸንፎ ያባርራቸዋል።”
የሙሴ መጠራት
2እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ 3ሁሉን የምችል አምላክ (ኤልሻዳይ) መሆኔን በማስረዳት ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ተገልጬላቸዋለሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በተሰኘው ቅዱስ ስሜ አማካይነት ግን አልተገለጥኩላቸውም። #ዘፍ. 17፥1፤ 28፥3፤ 35፥11፤ ዘፀ. 3፥13-15። 4እንደ ስደተኞች ሆነው የሚኖሩባትን የከነዓንን ምድር ላወርሳቸው ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ። 5እነሆ፥ አሁንም ግብጻውያን ባርያዎች አድርገው የሚያስጨንቁአቸውን የእስራኤላውያንን መራራ ጩኸት ሰምቼአለሁ፤ የገባሁትንም ቃል ኪዳን አስታውሼአለሁ። 6ስለዚህም ለእስራኤላውያን የምለውን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ግብጻውያን ከሚያደርሱባችሁ የባርነት ጭቈና በማዳን ነጻ አወጣችኋለሁ፤ አሠቃቂ ቅጣት አመጣባቸው ዘንድ የኀይል ክንዴን በእነርሱ ላይ አነሣለሁ፤ እናንተንም እታደጋችኋለሁ፤ 7የእኔ ሕዝብ አደርጋችኋለሁ፤ እኔም አምላካችሁ እሆናለሁ፤ ከግብጽ ባርነትም ነጻ በማወጣችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ መሆኔን ታውቃላችሁ፤ 8ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ አወርሳቸው ዘንድ በመሐላ ቃል ኪዳን ወደገባሁባት ምድር አመጣችኋለሁ፤ ርስትም አድርጌ አወርሳችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ” 9ሙሴም ይህን ሁሉ ለእስራኤላውያን ነገረ፤ እነርሱ ግን በወደቀባቸው ጨካኝ ጭቈና ምክንያት መንፈሳቸው ተሰብሮ ስለ ነበረ ሊያዳምጡት አልፈለጉም።
10እንደገናም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 11“ወደ ግብጽ ንጉሥ ሄደህ እስራኤላውያንን ከአገርህ እንዲወጡ ልቀቃቸው ብለህ ንገረው።”
12ነገር ግን ሙሴ “ወገኖቼ እስራኤላውያን እንኳ አልሰሙኝም፤ ታዲያ፥ ንጉሡ እንዴት ሊሰማኝ ይችላል? እንደምታየኝ እኔ ኰልታፋ ነኝ” ሲል መለሰ።
13እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን “እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር መርታችሁ እንድታወጡ እኔ ያዘዝኳችሁ መሆኔን ለእስራኤላውያንና ለግብጽ ንጉሥ ንገሩ” ብሎ አዘዛቸው።
የሙሴና የአሮን ትውልድ
14የያዕቆብ በኲር ልጅ ሮቤል፥ ሐኖክ፥ ፋሉ፥ ሔጽሮንና ካርሚ የሚባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህም በየስማቸው የሮቤል ነገድ አባቶች ናቸው። 15ስምዖን ከከነዓናዊት ሴት የተወለደውን ሻኡልን ጨምሮ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ ያኪንና፥ ጾሓር የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህም በየስማቸው የስምዖን ነገድ አባቶች ናቸው። 16ሌዊ ጌርሾን፥ ቀዓትና መራሪ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህም በየስማቸው የሌዊ ነገድ አባቶች ናቸው፤ ሌዊ በሕይወት የኖረበት ዘመን 137 ዓመት ነበር። 17ጌርሾን፥ ሊብኒና ሺምዒ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ብዙ ዘሮች ነበሩአቸው። 18ቀዓት፥ ዓምራም፥ ይጽሐር፥ ኬብሮንና ዑዚኤል የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ቀዓት በሕይወት የኖረበት ዘመን 133 ዓመት ነው። 19መራሪ ማሕሊና ሙሺ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህና ዘሮቻቸው ሁሉ የሌዊ ወገኖች ናቸው። #ዘኍ. 3፥17-20፤ 26፥57-58፤ 1ዜ.መ. 6፥16-19።
20ዓምራም ዮኬቤድ የተባለችውን የአባቱን እኅት አገባ፤ እርስዋም አሮንንና ሙሴን ወለደችለት። ዓምራም በሕይወት የኖረበት ዘመን 137 ዓመት ነው። 21ይጽሐር ቆሬ፥ ኔፌግና ዚክሪ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ 22ዑዚኤልም ሚሻኤል፥ ኤልጻፋንና ሲትሪ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት።
23አሮን የነአሶን እኅት የሆነችውን የዓሚናዳብን ልጅ ኤሊሼባን አገባ፤ እርስዋም ናዳብ፥ አቢሁ፥ አልዓዛርና ኢታማር የተባሉትን ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 24ቆሬ አሲር፥ ኤልቃናና አቢያሳፍ የተባሉ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነዚህም ለቆሬ ዘሮች ሁሉ የነገድ አባቶች ነበሩ። 25የአሮን ልጅ አልዓዛር የፑቲኤልን ልጅ አገባ፤ እርስዋም ፊኒሐስን ወለደችለት፤ እነዚህ ሁሉ የሌዊ የነገድ አባቶችና አለቆች ነበሩ።
26ከነዚህ መካከል እግዚአብሔር ሙሴና አሮን “የእስራኤልን ሕዝብ በየነገዳቸው ከግብጽ ምድር መርታችሁ አውጡ” ብሎ ያዘዛቸው ነው። 27“የእስራኤልን ሕዝብ ልቀቅ” ብለው ከግብጽ ንጉሥ ጋር የተነጋገሩ እነርሱ ናቸው።
እግዚአብሔር ለሙሴና ለአሮን የሰጠው ትእዛዝ
28እግዚአብሔር ሙሴን በግብጽ ምድር በተናገረው ጊዜ፤ 29“እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እኔ የምነግርህን ሁሉ ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር” አለው።
30ሙሴ ግን “እኔ ኰልታፋ ነኝ፤ ታዲያ፥ ንጉሡ እንዴት ሊሰማኝ ይችላል?” ሲል መለሰ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 6: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997