ኦሪት ዘጸአት 24:3-8
ኦሪት ዘጸአት 24:3-8 አማ05
ሙሴም ሄዶ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሥርዓት ሁሉ ለሕዝቡ ነገረ፤ ሕዝቡም በአንድነት “እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ እናደርጋለን” ሲል መለሰ። ሙሴም የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ሁሉ ጻፈ፤ በማግስቱም ጠዋት በማለዳ በተራራው ሥር መሠዊያ ሠራ፤ ለእያንዳንዱም የእስራኤል ነገድ አንድ የድንጋይ ዐምድ አኖረ፤ የሚቃጠል መሥዋዕት ወስደው ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ወጣቶች ወንዶችን ላከ፤ እነርሱም ወይፈኖችን የአንድነት መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። ሙሴም ከእንስሶቹ ደም ከፊሉን ወስዶ በገበቴ ውስጥ አኖረው፤ እኩሌታውንም በመሠዊያው ፊት ረጨው። ከዚህ በኋላ የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ድምፁን ከፍ በማድረግ ለሕዝቡ አነበበ፤ ሕዝቡም “ለእግዚአብሔር እንታዘዛለን እርሱ ያዘዘውንም ሁሉ እንፈጽማለን” አሉ። ከዚህ በኋላ ሙሴ በገበቴ ያለውን ደም ወስዶ በሕዝቡ ላይ በመርጨት “ይህ እንግዲህ እግዚአብሔር እነዚህን ሁሉ ትእዛዞች በሰጣችሁ ጊዜ ከእናንተ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የሚያጸናበት ደም ነው” አለ።

