የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 15:19-27

ኦሪት ዘጸአት 15:19-27 አማ05

“እስራኤላውያን በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻገሩ፤ የፈርዖን ፈረሶች፥ ሠረገሎችና ፈረሰኞቹ ሁሉ ወደ ባሕር በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ውሃውን መለሰባቸው።” የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያም ከበሮዋን አነሣች፤ ሌሎችም ሴቶች ከበሮዎቻቸውን እየመቱና እየጨፈሩ ይከተሉአት ጀመር፤ ማርያምም፥ “ፈረሱንና ፈረሰኛውን ወደ ባሕር በመጣል ክብር የተመላ ድልን ስለ ተጐናጸፈ፥ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” እያለች ዘመረችላቸው። ከዚህ በኋላ ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ከቀይ ባሕር አሳልፎ ወደ ሱር በረሓ መራቸው፤ ሦስት ቀን ሙሉ በበረሓ ተጓዙ፤ ነገር ግን ምንም ውሃ አላገኙም። ከዚህ በኋላ ማራ ወደ ተባለ ስፍራ በደረሱ ጊዜ ውሃው መራራ ስለ ነበረ ሊጠጡት አልቻሉም፤ ማራ ተብሎ የተጠራበትም ምክንያት ይኸው ነበር። ሕዝቡም በሙሴ ላይ በማጒረምረም “እንግዲህ ምን ልንጠጣ ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ሙሴም በብርቱ ጩኸት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አንድ እንጨት አሳየው፤ እርሱንም ወስዶ በውሃው ላይ በጣለው ጊዜ፥ ውሃው ወደጣፋጭነት ተለወጠ። በዚያ ስፍራ እግዚአብሔር የሚተዳደሩበት ደንብና ሥርዓት ሰጣቸው፤ በዚያም ፈተናቸው። እንዲህም አላቸው፤ “በጥሞና ትእዛዞቼን ብታዳምጡና በፊቴ መልካም የሆነውን ነገር በታዛዥነት ብታደርጉ፥ ኅጎቼንም ሁሉ ብትጠበቁ፥ በግብጻውያን ላይ ካመጣሁባቸው በሽታዎች በአንዱ እንኳ አልቀጣችሁም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” ከዚህ በኋላ ወደ ኤሊም መጡ፤ በዚያም ስፍራ ዐሥራ ሁለት የውሃ ምንጮችና ሰባ የተምር ዛፎች ነበሩ፤ ሕዝቡም በዚያ ከውሃው አጠገብ ሰፈሩ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}