ዘፀአት 15:19-27
ዘፀአት 15:19-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹና ከፈረሰኞቹ ጋር ወደ ባሕር ገቡ፤ እግዚአብሔርም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በየብስ አለፉ፤ ውኃውም ለእነርሱ በቀኝ እንደ ግድግዳ፥ በግራም እንደ ግድግዳ ሆነላቸው።” የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዝማሬ በኋላዋ ወጡ። ማርያምም አስቀድማ ለእግዚአብሔር እንዘምር አለች፥ “ለእግዚአብሔር እንዘምር በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ብሎአልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጥሎአልና።” ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ከኤርትራ ባሕር አውጥቶ ወደ ሱር ምድረ በዳ ወሰዳቸው። በምድረ በዳም ሦስት ቀን ተጓዙ፤ ይጠጡም ዘንድ ውኃ አላገኙም። ወደ ማራም በመጡ ጊዜ ከማራ ውኃ ሊጠጡ አልቻሉም፤ ውኃው መራራ ነበርና፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም “መሪር” ተብሎ ተጠራ። ሕዝቡም፥ “ምን እንጠጣለን?” ብለው በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ዕንጨትን አሳየው፤ በውኃውም ላይ ጣለው፤ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዐትንና ፍርድን አደረገላቸው፤ በዚያም ፈተናቸው። እርሱም፥ “አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥ በፊቱም መልካምን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና” አለ። እነርሱም ወደ ኤሎም መጡ፤ በዚያም ዐሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ነበሩባት፤ በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ።
ዘፀአት 15:19-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የፈርዖን ፈረሶች፣ ሠረገሎቹና ፈረሰኞቹ ወደ ባሕሩ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) የባሕሩን ውሃ በላያቸው ላይ መለሰባቸው፤ እስራኤላውያን ግን በባሕሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ተሻገሩ። ከዚያም የአሮን እኅት ነቢዪቱ ማርያም ከበሮዋን አንሥታ ያዘች፤ የቀሩትም ሴቶች ሁሉ ከበሮ ይዘው እያሸበሸቡ ተከተሏት። ማርያምም፣ “ፈረሱንና ፈረሰኛውን፣ በባሕር ውስጥ ጥሏል፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘምሩ፤ እጅግ ከፍ ከፍ ብሏልና” እያለች ዘመረችላቸው። ከዚያም ሙሴ እስራኤልን ከቀይ ባሕር እየመራቸው ወደ ሱር ምድረ በዳ ሄዱ፤ ለሦስት ቀናት ውሃ ሳያገኙም በምድረ በዳ ተጓዙ። ማራ በደረሱ ጊዜ ውሃው መራራ ስለ ነበር ሊጠጡት አልቻሉም፤ ቦታው ማራ ተብሎ የተጠራውም ከዚህ የተነሣ ነው። ሕዝቡም በሙሴ ላይ በማጕረምረም፣ “ምን እንጠጣ?” አሉ። ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) አንዲት ዛፍ አሳየው፤ ዕንጨቷንም ወደ ውሃው ጣላት፤ ውሃውም ጣፋጭ ሆነ። በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሕግና ሥርዐት አበጀላቸው፤ በዚያም ስፍራ ፈተናቸው። እርሱም አለ፤ “የአምላካችሁን እግዚአብሔር (ያህዌ) ድምፅ በጥንቃቄ ብትሰሙ፣ በፊቱም ትክክል የሆነውን ብትፈጽሙ፣ ትእዛዞቹን ልብ ብትሉና ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቁ፣ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁባቸውን ማንኛውንም ዐይነት በሽታ በእናንተ ላይ አላመጣም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝና።” ከዚያም ዐሥራ ሁለት ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ወዳሉበት ወደ ኤሊም መጡ፤ እነርሱም በውሃው አጠገብ በዚያ ሰፈሩ።
ዘፀአት 15:19-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹ ከፈረሰኞቹም ጋር ወደ ባሕር ገቡ፥ እግዚአብሔርም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በየብስ ሄዱ። የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ። ማርያምም እየዘመረች መለሰችላቸው፦ በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ሙሴም እስራኤልን ከኤርትራ ባሕር አስጓዘ፥ ወደ ሱርም ምድረ በዳ ወጡ፤ በምድረ በዳም ሦስት ቀን ሄዱ፥ ውኃም አላገኙም። ወደ ማራም በመጡ ጊዜ የማራ ውኃ መራራ ነበረና ሊጠጡ አልቻሉም፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም ማራ ተብሎ ተጠራ። ሕዝቡም፦ ምን እንጠጣለን? ብለው በሙሴ ላይ አንጎራጎሩ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም እንጨትን አሳየው፥ በውኃውም ላይ ጣለው፥ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤ እርሱም፦ አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና አለ። እነርሱም ወደ ኤሊም መጡ፥ በዚያም አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ነበሩባት፤ በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ።
ዘፀአት 15:19-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“እስራኤላውያን በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻገሩ፤ የፈርዖን ፈረሶች፥ ሠረገሎችና ፈረሰኞቹ ሁሉ ወደ ባሕር በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ውሃውን መለሰባቸው።” የአሮን እኅት ነቢይቱ ማርያም ከበሮዋን አነሣች፤ ሌሎችም ሴቶች ከበሮዎቻቸውን እየመቱና እየጨፈሩ ይከተሉአት ጀመር፤ ማርያምም፥ “ፈረሱንና ፈረሰኛውን ወደ ባሕር በመጣል ክብር የተመላ ድልን ስለ ተጐናጸፈ፥ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” እያለች ዘመረችላቸው። ከዚህ በኋላ ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ከቀይ ባሕር አሳልፎ ወደ ሱር በረሓ መራቸው፤ ሦስት ቀን ሙሉ በበረሓ ተጓዙ፤ ነገር ግን ምንም ውሃ አላገኙም። ከዚህ በኋላ ማራ ወደ ተባለ ስፍራ በደረሱ ጊዜ ውሃው መራራ ስለ ነበረ ሊጠጡት አልቻሉም፤ ማራ ተብሎ የተጠራበትም ምክንያት ይኸው ነበር። ሕዝቡም በሙሴ ላይ በማጒረምረም “እንግዲህ ምን ልንጠጣ ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ሙሴም በብርቱ ጩኸት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አንድ እንጨት አሳየው፤ እርሱንም ወስዶ በውሃው ላይ በጣለው ጊዜ፥ ውሃው ወደጣፋጭነት ተለወጠ። በዚያ ስፍራ እግዚአብሔር የሚተዳደሩበት ደንብና ሥርዓት ሰጣቸው፤ በዚያም ፈተናቸው። እንዲህም አላቸው፤ “በጥሞና ትእዛዞቼን ብታዳምጡና በፊቴ መልካም የሆነውን ነገር በታዛዥነት ብታደርጉ፥ ኅጎቼንም ሁሉ ብትጠበቁ፥ በግብጻውያን ላይ ካመጣሁባቸው በሽታዎች በአንዱ እንኳ አልቀጣችሁም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” ከዚህ በኋላ ወደ ኤሊም መጡ፤ በዚያም ስፍራ ዐሥራ ሁለት የውሃ ምንጮችና ሰባ የተምር ዛፎች ነበሩ፤ ሕዝቡም በዚያ ከውሃው አጠገብ ሰፈሩ።
ዘፀአት 15:19-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹ ከፈረሰኞቹም ጋር ወደ ባሕር ገቡ፥ ጌታም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በደረቅ ምድር ሄዱ። የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ ከበሮ በመያዝና በጭፈራ በኋላዋ ወጡ። ማርያምም፦ “ለጌታ ዘምሩ በክብር ከፍ ከፍ ብሏልና፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ” እያለች ዘመረችላቸው። ሙሴም እስራኤልን ከቀይ ባሕር መራ፥ ወደ ሹር ምድረ በዳም ሄዱ፤ በምድረ በዳም ሦስት ቀን ሄዱ፥ ውኃም አላገኙም። ወደ ማራም መጡ፥ የማራንም ውኃ ሊጠጡ አልቻሉም መራራ ነበረና፤ ስለዚህ አንድ ሰው ማራ ብሎ ጠራው። ሕዝቡም፦ “ምን እንጠጣለን?” ብለው በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። እርሱም ወደ ጌታ ጮኸ፤ ጌታም ዛፍ አሳየው፥ በውኃውም ላይ ጣለው፥ ውኃውም ጣፋጭ ሆነ። ጌታም በዚያ ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤ እርሱም፦ “አንተ የጌታ አምላክህን ቃል ብትሰማ፥ በፊቱም ትክክል የሆነውን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላመጣብህም፤ ፈዋሽህ እኔ ጌታ ነኝና” አለ። እነርሱም ወደ ኤሊም መጡ፥ በዚያም ዐሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የተምር ዛፎች ነበሩ፤ በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ።