የፈርዖን ፈረሶች፣ ሠረገሎቹና ፈረሰኞቹ ወደ ባሕሩ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) የባሕሩን ውሃ በላያቸው ላይ መለሰባቸው፤ እስራኤላውያን ግን በባሕሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ተሻገሩ። ከዚያም የአሮን እኅት ነቢዪቱ ማርያም ከበሮዋን አንሥታ ያዘች፤ የቀሩትም ሴቶች ሁሉ ከበሮ ይዘው እያሸበሸቡ ተከተሏት። ማርያምም፣ “ፈረሱንና ፈረሰኛውን፣ በባሕር ውስጥ ጥሏል፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘምሩ፤ እጅግ ከፍ ከፍ ብሏልና” እያለች ዘመረችላቸው። ከዚያም ሙሴ እስራኤልን ከቀይ ባሕር እየመራቸው ወደ ሱር ምድረ በዳ ሄዱ፤ ለሦስት ቀናት ውሃ ሳያገኙም በምድረ በዳ ተጓዙ። ማራ በደረሱ ጊዜ ውሃው መራራ ስለ ነበር ሊጠጡት አልቻሉም፤ ቦታው ማራ ተብሎ የተጠራውም ከዚህ የተነሣ ነው። ሕዝቡም በሙሴ ላይ በማጕረምረም፣ “ምን እንጠጣ?” አሉ። ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) አንዲት ዛፍ አሳየው፤ ዕንጨቷንም ወደ ውሃው ጣላት፤ ውሃውም ጣፋጭ ሆነ። በዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሕግና ሥርዐት አበጀላቸው፤ በዚያም ስፍራ ፈተናቸው። እርሱም አለ፤ “የአምላካችሁን እግዚአብሔር (ያህዌ) ድምፅ በጥንቃቄ ብትሰሙ፣ በፊቱም ትክክል የሆነውን ብትፈጽሙ፣ ትእዛዞቹን ልብ ብትሉና ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቁ፣ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁባቸውን ማንኛውንም ዐይነት በሽታ በእናንተ ላይ አላመጣም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝና።” ከዚያም ዐሥራ ሁለት ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ወዳሉበት ወደ ኤሊም መጡ፤ እነርሱም በውሃው አጠገብ በዚያ ሰፈሩ።
ዘፀአት 15 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፀአት 15
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፀአት 15:19-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos