ንጉሡም ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “አምላካችሁን እግዚአብሔርንና እናንተን በድያለሁ፤ እንግዲህስ እነሆ፥ አንድ ጊዜ ብቻ በደሌን ይቅር እንድትሉኝ እለምናችኋለሁ፤ ይህን ከባድ ቅጣት ከእኔ እንዲያስወግድም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለምኑልኝ።” ሙሴም ከንጉሡ ፊት ወጥቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። እግዚአብሔርም የምሥራቁን ነፋስ የሚቋቋምና አንበጦቹንም ጠራርጎ ወደ ቀይ ባሕር የሚነዳ ብርቱ ነፋስ ከምዕራብ በኩል አስነሣ፤ በዚህ ዐይነት በመላው የግብጽ ምድር አንድ አንበጣ እንኳ አልቀረም። ነገር ግን እግዚአብሔር የንጉሡን ልብ ስላደነደነ አሁንም እስራኤላውያንን አለቀቀም። ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን “እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋው፤ በእጅ እስከሚዳሰስ ድረስ ጥቅጥቅ ያለ ጨለማ የግብጽን ምድር ይሸፍናል” አለው። ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በመላውም የግብጽ ምድር ለሦስት ቀን ጨለማ ሆነ። ግብጻውያን እርስ በርሳቸው ስለማይተያዩ ማንም ሰው እስከ ሦስት ቀን ከቤቱ መውጣት አልቻለም ነበር፤ እስራኤላውያን በሚኖሩበት ስፍራ ግን ብርሃን ነበር። ንጉሡም ሙሴን ጠርቶ “ሄዳችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁም ከእናንተ ጋር መሄድ ይችላሉ፤ ነገር ግን በጎቻችሁና ፍየሎቻችሁ የቀንድ ከብቶቻችሁም እዚህ መቅረት ይኖርባቸዋል።” ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እንዲህ ከሆነማ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም መሥዋዕት የምናቀርባቸው እንስሶች አንተ ትሰጠናለህ ማለት ነዋ? ከቶ ይህ ሊሆን አይችልም፤ እንስሶቻችንን ሁሉ እንወስዳለን፤ አንዲት ሰኮና እንኳ ወደ ኋላ አትቀርም፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን የምናገለግልባቸውን እንስሶች መርጠን ማቅረብ ያለብን እኛው ራሳችን ነን፤ እዚያም ከመድረሳችን በፊት ለእርሱ የምንሠዋቸው እንስሶች ምን ዐይነት እንደ ሆኑ ማወቅ አንችልም።” እግዚአብሔርም የንጉሡን ልብ ስላደነደነ ሕዝቡን መልቀቅ አልፈለገም፤ ስለዚህ ሙሴን “ዳግመኛ እንዳላይህ ከፊቴ ወዲያ ሂድ! እኔን በምታይበት ጊዜ እንደምትሞት ዕወቅ!” አለው። ሙሴም “እውነት ነው፤ አንተ እንዳልከው ዳግመኛ አላይህም” አለው።
ኦሪት ዘጸአት 10 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 10:16-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች