ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነሆ እንደገና ወደ ፈርዖን ተመልሰህ ግባ፤ እኔ የእርሱንና የመኳንንቱን ልብ ያደነደንኩት በመካከላቸው እነዚህን ተአምራት ለማድረግ ዐቅጄ ነው፤ እንዲሁም እነዚህን ተአምራት ባደረግሁ ጊዜ ግብጻውያንን እንዴት እንደቀጣሁ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ መንገር ትችሉ ዘንድ ነው፤ በዚህም ዐይነት ሁላችሁም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።” ስለዚህ ሙሴና አሮን ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉት፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለእኔ መታዘዝን እምቢ የምትለው እስከ መቼ ነው? አሁንም ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤ በእምቢተኛነትህ ብትጸና ግን እነሆ፥ በነገው ቀን የአንበጣ መንጋ በአገርህ ላይ እንዲመጣ አደርጋለሁ። የአንበጣውም መንጋ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሣ ምድሪቱን በመላ ይሸፍናል፤ ከበረዶው የተረፈውን ነገር፥ ዛፉን ሁሉ ምንም ሳይቀር ይበላዋል። ቤተ መንግሥትህን፥ የመኳንንትህንና የሕዝብህን ቤቶች ሁሉ የአንበጣ መንጋ ይሞላዋል፤ ይህም ሁኔታ ከቀድሞ አባቶችህ ዘመን እስከ አሁን ከታየው መከራ ሁሉ የከፋ ይሆናል።’ ” ሙሴም ከፈርዖን ፊት ወጥቶ ሄደ። መኳንንቱም ንጉሡን እንዲህ አሉት፤ “ይህ ሰው ለእኛ ወጥመድ ሆኖ የሚያስቸግረን እስከ መቼ ነው? አምላካቸውን እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ከእስራኤላውያን ወገን ወንዶቹ ይሂዱ፤ አገሪቱ በመጥፋት ላይ መሆንዋ አይታወቅህምን?” ስለዚህ ሙሴና አሮን ተጠርተው ወደ ንጉሡ ቀረቡ፤ ንጉሡም “ሄዳችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁን ማገልገል ትችላላችሁ፤ ነገር ግን መሄድ የሚገባቸው የትኞቹ ናቸው?” አላቸው። ሙሴም “ሕፃን ልጆቻችንና ሽማግሌዎቻችን ሳይቀሩ ሁላችንም እንሄዳለን፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንን፥ በጎቻችንንና ፍየሎቻችንን፥ የቀንድ ከብቶቻችንንም ሁሉ እንወስዳለን፤ በምንሄድበት ስፍራ ለእግዚአብሔር በዓል እናደርጋለን” ሲል መለሰ። ንጉሡም እንዲህ አለ፦ “እስቲ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ የዐመፅ ሤራ ማቀዳችሁ ግልጥ ስለ ሆነ ሴቶቻችሁንና ልጆቻችሁን ይዛችሁ እንድትሄዱ አልፈቅድላችሁም! እንግዲህ እግዚአብሔርን ማገልገል ከፈለጋችሁ ወንዶቹ ብቻ መሄድ ትችላላችሁ”። ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ተባረው ወጡ። እግዚአብሔርም ሙሴን “አንበጦችን ለማምጣት እጅህን በግብጽ ምድር ላይ ዘርጋ፤ እነርሱም መጥተው ቡቃያውን ሁሉና ከበረዶ የተረፈውን ተክል ሁሉ ይበላሉ” አለው። ስለዚህ ሙሴ በግብጽ ምድር ላይ እጁን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም በዚያን ቀንና ሌሊት የምሥራቅ ነፋስ አስነሣ፤ በነጋም ጊዜ ያ የምሥራቅ ነፋስ አንበጦችን አመጣ። እነርሱም በመርመስመስ መጥተው አገሪቱን ወረሩ፤ ይህን ያኽል ብዛት ያለው የአንበጣ መንጋ ከዚያ በፊት ታይቶ አይታወቅም፤ ወደ ፊትም ሊታይ አይችልም። አገሪቱ ጠቊራ ጨለማ እስክትመስል ድረስ የአንበጣ መንጋ ሸፈናት፤ አንድም ነገር ሳያስቀር ከበረዶ የተረፈውን በየዛፉ ላይ የሚገኘውን ፍሬና ሌላውንም ተክል ሁሉ ግጦ በላው፤ በግብጽ ምድር ከሚገኘው ከማንኛውም ዛፍና ተክል ለምለም የሆነውን ቅጠል ሁሉ መድምዶ በላ።
ኦሪት ዘጸአት 10 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 10:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች