ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ተመልሰህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች በመካከላቸው ለማድረግ የፈርዖንንና የሹማምቱን ልብ አደንድኛለሁና፤ ይኸውም ግብጻውያንን እንዴት አድርጌ እንደ ቀጣኋቸውና በመካከላቸውም ምልክቶቼን እንዴት እንዳደረግሁ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ እንድትነግሩና እኔ እግዚአብሔር መሆኔንም እንድታውቁ ነው።” ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እንዲህ አሉት፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ራስህን በፊቴ ለማዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ሕዝቤ ያመልኩኝ ዘንድ ልቀቃቸው። እንዳይሄዱ ብትከለክላቸው ነገ በአገርህ ላይ አንበጣዎችን አመጣለሁ። አንበጣዎቹም ምድሪቱ እስከማትታይ ድረስ ይሸፍኗታል፤ በመስክህ ላይ እያቈጠቈጠ ያለውን ዛፍ ሁሉ ሳይቀር ከበረዶ የተረፈውንም ጥቂቱን ሁሉ ይበሉታል። የአንተን፣ የሹማምትህንና የግብጻውያንን ቤቶች ሁሉ ይሞሏቸዋል፤ ይህም አባቶችህም ሆኑ ቅድመ አያቶችህ በዚህች ምድር ከሰፈሩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከቶ አይተውት የማያውቁት ነው።’ ” ሙሴም ተመለሰና ከፈርዖን ተለይቶ ሄደ። የፈርዖንም ሹማምት፣ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ሰዎቹን ልቀቃቸውና ይሂዱ። ግብጽ መጥፋቷን እስካሁን አልተገነዘብህምን?” አሉት። ከዚያም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን እንዲመጡ ተደረገ፤ “ሂዱ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ነገር ግን መሄድ የሚገባቸው የትኞቹ ናቸው?” አለ። ሙሴም፣ “ለእግዚአብሔር በዓል ልናከብር ስለ ሆነ ወጣቶቻችንንና ሽማግሌዎቻችንን፣ ወንድና ሴት ልጆቻችንን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችንን እንዲሁም የቀንድ ከብቶቻችንን ይዘን እንሄዳለን” አለ። ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ከሴቶቻችሁና ከልጆቻችሁ ጋራ እንድትሄዱ እለቅቃችኋለሁ፤ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ይሁን፤ ነገር ግን ተንኰል ዐስባችኋል። አይሆንም፤ ወንዶቹ ብቻ እንዲሄዱና እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አድርጉ፤ የጠየቃችሁት ይህንኑ ነው።” ከዚያም ሙሴና አሮን ከፈርዖን ፊት እንዲወጡ ተደረገ። እግዚአብሔር ሙሴን፣ “የአንበጣ መንጋ ምድሪቱን እንዲወርር ከበረዶ የተረፈውን ሁሉና በማሳም ላይ የበቀለውን ሁሉ ጠርጎ እንዲበላ እጅህን በግብጽ አገር ላይ ዘርጋ” አለው። ስለዚህ ሙሴ በግብጽ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም በዚያ ቀንና ሌሊት በሙሉ በምድሪቱ ላይ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ በማግስቱም ነፋሱ አንበጣዎችን አመጣ። እነርሱም ግብጽን በሙሉ ወረሩ፤ ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሆነው የሀገሪቱን ዳር ድንበር ሁሉ አለበሱ። እንዲህ ያለ የአንበጣ መዓት ከዚህ ቀደም አልነበረም፤ ወደ ፊትም ደግሞ አይኖርም። ምድሩ ሁሉ ጠቍሮ እስኪጨልም ድረስ አለበሱት። ከበረዶ የተረፈውን፣ በመስክ ላይ የበቀለውንና በዛፍ ላይ ያለውን ፍሬ ሁሉ ጠርገው በሉ። በግብጽ ምድር ሁሉ በዛፍ ላይ ወይም በተክል ላይ አንዳች ቅጠል አልተረፈም ነበር።
ዘፀአት 10 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፀአት 10
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፀአት 10:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች