መጽሐፈ አስቴር 9:20-32

መጽሐፈ አስቴር 9:20-32 አማ05

መርዶክዮስም የዚህን ሁሉ ድርጊት ታሪክ ጽፎ በመላው የፋርስ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛት ውስጥ በቅርብም በሩቅም ወደሚኖሩት አይሁድ ሁሉ በደብዳቤ ላከው። በየዓመቱ የአዳርን ወር ዐሥራ አራተኛና ዐሥራ አምስተኛ ቀን በዓል አድርገው በማክበር እንዲጠብቁት ነገራቸው። እነዚህም ዕለቶች አይሁድ ራሳቸውን ከጠላቶቻቸው እጅ በማዳን ዕረፍት ያገኙባቸው ቀኖች ናቸው፤ ከሐዘንና ከተስፋ መቊረጥ ወደ ደስታና ወደ ሐሴት የተላለፉት በዚህ ወር ነበር፤ በእነዚህ ዕለቶች በዓል አድርገው በመብላትና በመጠጣት እየተደሰቱ፥ እርስ በርሳቸው አንዳቸው ለሌላው የምግብ ስጦታ እየተለዋወጡና ለድኾችም ስጦታ እየሰጡ እንዲጠብቁአቸው ተነገራቸው። ስለዚህም አይሁድ የመርዶክዮስን መመሪያ በመቀበል በዚህ ሁኔታ የተጀመረው በዓል በየዓመቱ እንዲከበር ለማድረግ ተስማሙ። የአይሁድ ጠላት የነበረው የአጋግ ዘር የሆነው የሃመዳታ ልጅ ሃማን፥ ፑሪም ተብለው የሚጠሩትን ዕጣዎች በመጣል አይሁድ በሙሉ ከምድረ ገጽ ጠራርጎ ለማጥፋት የሚችልበትን ዕለት ለማወቅ ዐቅዶ ነበር። ነገር ግን አስቴር ወደ ንጉሡ ቀረበች፤ ንጉሡም ትእዛዙን በጽሑፍ እንዲተላለፍ አደረገ፤ ያም ትእዛዝ ባስገኘው ውጤት ሃማን አይሁድን ለመደምሰስ ዐቅዶት የነበረው ሤራ በራሱ ላይ እንዲመለስበት ሆነ፤ እርሱና ዐሥር ልጆቹ በእንጨት ላይ ተሰቀሉ። እነዚህ የበዓላት ቀኖች “ፑሪም” ተብለው የሚጠሩትም በዚሁ ምክንያት ነው፤ መርዶክዮስ የላከውን ደብዳቤ መሠረት በማድረግና በዐይናቸው ያዩትንና የደረሰባቸውንም ነገር ሁሉ በማስታውስ፥ አይሁድ ለራሳቸው፥ ለዘሮቻቸው አይሁዳዊ መሆን ለሚፈልግ ሁሉ ቋሚ ደንብ አደረጉ፤ ይኸውም በየዓመቱ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ መርዶክዮስ በሰጠው መመሪያ መሠረት እነዚህ ሁለት ቀኖች ባለማቋረጥ ይከበራሉ። እነዚህ የፑሪም ቀኖች በየትውልዱ፥ በየቤተሰቡ፥ በየሀገሩና በየከተማው መከበር እንዳለባቸው ተወሰነ፤ እነዚህም ቀኞች ሳይከበሩ መቅረት የለባቸውም፤ ከትውልዱም መካከል መታሰቢያነታቸው መቋረጥ የለበትም። ከዚህም ሁሉ በኋላ የአቢኀይል ልጅ ንግሥት አስቴር ከመርዶክዮስ ጋር በመተባበር ስለ ፑሪም፥ መርዶክዮስ ቀደም ሲል የላከውን ደብዳቤ በማጠናከር ያላትን ሥልጣን የሚገልጥ ትእዛዝ ያለበት ደብዳቤ ጽፋ ላከች። ደብዳቤውም በአይሁድ አድራሻ የተጻፈ ሲሆን ቅጂው ግን በፋርስ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛት ውስጥ ላሉት ለመቶ ኻያ ሰባት አገሮች ሁሉ ተልኮ ነበር፤ የደብዳቤውም መልእክት ለአይሁድ ሰላምንና በደኅንነት የመኖርን መልካም ምኞት የሚገልጥ ነበር። ከዚህም ጋር ከአሁን በፊት ለጾምና ለሐዘን ደንብ አውጥተው በነበረው ዐይነት እነዚህን የፑሪም ዕለቶች እነርሱ ራሳቸውም ሆኑ ወደፊት የሚነሡት ዘሮቻቸው በየዓመቱ በማክበር ይጠብቁአቸው ዘንድ ይጠይቃል፤ ይህም ንግሥት አስቴርና መርዶክዮስ በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ሁለቱም ያስተላለፉት ትእዛዝ ነበር። ስለ ፑሪም ሕግና ሥርዓት የተነገረውን ለማጠናከር ንግሥት አስቴር የላከችው የደብዳቤ ትእዛዝ በልዩ የብራና ጥቅል እንዲጻፍ ተደረገ።