መጽሐፈ አስቴር 6:1-10

መጽሐፈ አስቴር 6:1-10 አማ05

በዚያኑ ሌሊት ንጉሡ እንቅልፍ አጥቶ ስለ ነበር በቤተ መንግሥቱ መዝገብ ላይ የሰፈሩትን የታሪክ ማስታወሻዎች አምጥተው ያነቡለት ዘንድ ትእዛዝ ሰጠ። ከተነበቡትም ማስታወሻዎች አንዱ ክፍል የንጉሡን መኖሪያ ክፍሎች ይጠብቁ የነበሩት ቢግታናና ቴሬሽ ተብለው የሚጠሩት ሁለቱ ጃንደረቦች ንጉሡን ለመግደል የጠነሰሱትን ሤራ መርዶክዮስ እንዴት እንደ ደረሰበት የሚገልጥ ነበር፤ ንጉሡም “ታዲያ፥ ይህን በማድረጉ ለመርዶክዮስ የሰጠነው ዕውቅናና ክብር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ። አገልጋዮቹም “ለእርሱ የተደረገለት ምንም ነገር የለም” ሲሉ መለሱለት። ንጉሡም “በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ከባለሥልጣኖቼ መካከል ማን አለ?” ሲል ጠየቀ። በዚህ ጊዜ ሃማን ባዘጋጀው እንጨት ላይ መርዶክዮስን ይሰቅል ዘንድ የንጉሡን ፈቃድ ለመጠየቅ ወደ ቤተ መንግሥቱ አደባባይ በመግባት ላይ ነበር፤ ስለዚህም አገልጋዮቹ “እነሆ ሃማን አንተን ለማነጋገር እየጠየቀ ነው” አሉት። ንጉሡም “ግባ በሉት” አለ። ሃማንም ወደ ውስጥ በገባ ጊዜ ንጉሡ “ታላቅ ክብር ልሰጠው የፈለግኹት አንድ ሰው አለ፤ ታዲያ ለዚህ ሰው ምን ላደርግለት የሚገባ ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀው። ሃማንም “ንጉሡ ይህን ክብር ከእኔ ሌላ ለማን ይሰጣል?” ብሎ በልቡ አሰበ። ስለዚህም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ለእንደዚህ ያለው ሰው አንተ ራስህ የለበስከውን ልብሰ መንግሥት እንዲያመጡለት አድርግ፤ አንተም በተቀመጥክበት ፈረስ ራስ ላይ የንጉሣዊ ዘውድ ምልክት እንዲያደርጉበት እዘዝ፤ ከልዑላን መሳፍንቱ አንዱን አስጠርተህ ልብሰ መንግሥቱን ይስጠውና በተዘጋጀለት ፈረስ ላይ አስቀምጦ ፊት ለፊት እየመራ ወደ ከተማይቱ አደባባይ እንዲያወጣው አድርግ፤ ሁለቱም በሚጓዙበት ጊዜ መስፍኑ ‘ንጉሡ ሊያከብረው የፈለገውን ሰው እንዴት እንደ ሸለመው ተመልከቱ!’ እያለ ዐዋጅ ይናገር።” ንጉሡም ሃማንን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “በል እንግዲህ ፍጠን፤ ልብሰ መንግሥቱንና ፈረሱን አዘጋጅተህ ይህን አሁን ያልከውን ክብር ሁሉ አይሁዳዊ ለሆነው ለመርዶክዮስ አድርግለት፤ እርሱንም አሁን በቤተ መንግሥቱ መግቢያ በር አጠገብ ስለምታገኘው ካሳሰብከው ነገር አንድም ሳይቀር ሁሉንም አድርግለት።”