በዚያች ሌሊት ንጉሡ እንቅልፍ መተኛት አልቻለም። ስለዚህ በዘመነ መንግሥቱ የተመዘገበው የታሪክ መጽሐፍ ቀርቦ እንዲነበብለት አዘዘ። በዚያም በሩን ከሚጠብቁት ከንጉሡ የጦር አዛዦች ሁለቱ፣ ገበታና ታራ ንጉሥ ጠረክሲስን ለመግደል አሢረው እንደ ነበርና ይህንም መርዶክዮስ እንደ ተናገረ ተጽፎ ተገኘ። ንጉሡም፣ “ታዲያ ይህን በማድረጉ መርዶክዮስ ያገኘው ክብርና ማዕርግ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ። የቅርብ አገልጋዮቹም፣ “ምንም አልተደረገለትም” ብለው መለሱ። ንጉሡም፣ “በአደባባዩ ማን አለ?” ሲል ጠየቀ። በዚህ ጊዜ ሐማ በተከለው ዕንጨት ላይ መርዶክዮስ ይሰቀል ዘንድ ለንጉሡ ለመናገር በውጭ በኩል ወደሚገኘው የቤተ መንግሥቱ አደባባይ ገና መድረሱ ነበር። የቅርብ አገልጋዮቹም፣ “እነሆ፤ ሐማ በአደባባዩ ቆሟል” አሉት። ንጉሡም፣ “ግባ በሉት” ብሎ አዘዘ። ሐማ በገባ ጊዜ ንጉሡ፣ “ንጉሥ ሊያከብረው ለወደደው ሰው ምን ሊደረግለት ይገባል?” ሲል ጠየቀው። በዚህ ጊዜ ሐማ፣ “ንጉሡ ከእኔ ይልቅ የሚያከብረው ማን አለ?” ሲል በልቡ ዐሰበ። ስለዚህ ሐማ ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ንጉሡ ሊያከብረው ለወደደው ሰው፣ ንጉሡ የሚጐናጸፈው ልብሰ መንግሥት፣ ንጉሡም የሚቀመጥበትና የንጉሡን ዘውድ በራሱ ላይ ያደረገ ፈረስ ይምጣለት። ከዚያም ልብሱና ፈረሱ እጅግ ከከበሩት ከንጉሡ ልዑላን መሳፍንት በአንዱ እጅ ይሰጥለት። ንጉሡ ሊያከብረው የወደደውን ሰው ያልብሱት፤ በፈረሱም ላይ አስቀምጠውም በከተማዪቱ ዋና ዋና መንገዶች ላይ እየመሩ፣ ‘ንጉሡ ሊያከብረው ለሚወድደው ሰው ይህ ተደርጎለታል’ ይበሉ።” ንጉሡም ሐማን፣ “በል ፈጥነህ ሂድ፤ ልብሱንና ፈረሱን ውሰድ፤ በንጉሡ በር ላይ ለሚቀመጠው ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስም ልክ እንዳልኸው አድርግለት፤ ከተናገርኸውም አንዳች ነገር እንዳይጐድል” ሲል አዘዘው።
አስቴር 6 ያንብቡ
ያዳምጡ አስቴር 6
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አስቴር 6:1-10
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች