መጽሐፈ አስቴር 6
6
ንጉሥ አርጤክስስ መርዶክዮስን እንደ ሾመ
1በዚያኑ ሌሊት ንጉሡ እንቅልፍ አጥቶ ስለ ነበር በቤተ መንግሥቱ መዝገብ ላይ የሰፈሩትን የታሪክ ማስታወሻዎች አምጥተው ያነቡለት ዘንድ ትእዛዝ ሰጠ። 2ከተነበቡትም ማስታወሻዎች አንዱ ክፍል የንጉሡን መኖሪያ ክፍሎች ይጠብቁ የነበሩት ቢግታናና ቴሬሽ ተብለው የሚጠሩት ሁለቱ ጃንደረቦች ንጉሡን ለመግደል የጠነሰሱትን ሤራ መርዶክዮስ እንዴት እንደ ደረሰበት የሚገልጥ ነበር፤ #አስ. 2፥21-22። 3ንጉሡም “ታዲያ፥ ይህን በማድረጉ ለመርዶክዮስ የሰጠነው ዕውቅናና ክብር ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።
አገልጋዮቹም “ለእርሱ የተደረገለት ምንም ነገር የለም” ሲሉ መለሱለት።
4ንጉሡም “በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ከባለሥልጣኖቼ መካከል ማን አለ?” ሲል ጠየቀ።
በዚህ ጊዜ ሃማን ባዘጋጀው እንጨት ላይ መርዶክዮስን ይሰቅል ዘንድ የንጉሡን ፈቃድ ለመጠየቅ ወደ ቤተ መንግሥቱ አደባባይ በመግባት ላይ ነበር፤ 5ስለዚህም አገልጋዮቹ “እነሆ ሃማን አንተን ለማነጋገር እየጠየቀ ነው” አሉት።
ንጉሡም “ግባ በሉት” አለ።
6ሃማንም ወደ ውስጥ በገባ ጊዜ ንጉሡ “ታላቅ ክብር ልሰጠው የፈለግኹት አንድ ሰው አለ፤ ታዲያ ለዚህ ሰው ምን ላደርግለት የሚገባ ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀው።
ሃማንም “ንጉሡ ይህን ክብር ከእኔ ሌላ ለማን ይሰጣል?” ብሎ በልቡ አሰበ።
7-8ስለዚህም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ለእንደዚህ ያለው ሰው አንተ ራስህ የለበስከውን ልብሰ መንግሥት እንዲያመጡለት አድርግ፤ አንተም በተቀመጥክበት ፈረስ ራስ ላይ የንጉሣዊ ዘውድ ምልክት እንዲያደርጉበት እዘዝ፤ 9ከልዑላን መሳፍንቱ አንዱን አስጠርተህ ልብሰ መንግሥቱን ይስጠውና በተዘጋጀለት ፈረስ ላይ አስቀምጦ ፊት ለፊት እየመራ ወደ ከተማይቱ አደባባይ እንዲያወጣው አድርግ፤ ሁለቱም በሚጓዙበት ጊዜ መስፍኑ ‘ንጉሡ ሊያከብረው የፈለገውን ሰው እንዴት እንደ ሸለመው ተመልከቱ!’ እያለ ዐዋጅ ይናገር።”
10ንጉሡም ሃማንን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “በል እንግዲህ ፍጠን፤ ልብሰ መንግሥቱንና ፈረሱን አዘጋጅተህ ይህን አሁን ያልከውን ክብር ሁሉ አይሁዳዊ ለሆነው ለመርዶክዮስ አድርግለት፤ እርሱንም አሁን በቤተ መንግሥቱ መግቢያ በር አጠገብ ስለምታገኘው ካሳሰብከው ነገር አንድም ሳይቀር ሁሉንም አድርግለት።”
11ስለዚህም ሃማን ልብሰ መንግሥትና ፈረስ አዘጋጅቶ መርዶክዮስን አለበሰው፤ መርዶክዮስ በፈረሱ ላይ ከተቀመጠም በኋላ ሃማን ፊት ፊት እየሄደ በመምራት “ንጉሡ ሊያከብረው የፈለገውን ሰው እንዴት እንደ ሸለመው ተመልከቱ!” እያለ ያውጅ ነበር።
12ከዚህ በኋላ መርዶክዮስ ወደ ቤተ መንግሥቱ መግቢያ ተመልሶ ሲሄድ፥ ሃማን ከኀፍረቱ ብዛት የተነሣ ራሱን በመከናነብ ወደ መኖሪያ ቤቱ ፈጥኖ ሄደ። 13ለሚስቱና ለወዳጆቹም የደረሰበትን አሳፋሪ ነገር በሙሉ ነገራቸው፤ ሚስቱና እነዚያ አስተዋዮች የሆኑ ወዳጆቹም “እነሆ በገዛ እጅህ ሥልጣንህን ለመርዶክዮስ ልታስረክብ ተቃርበሃል፤ እርሱ አይሁዳዊ ስለ ሆነ ልትቋቋመው አትችልም፤ በእርግጥም እርሱ ያሸንፍሃል!” አሉት።
በሃማን ላይ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት
14እነርሱም ገና ይህን በመነጋገር ላይ ሳሉ የቤተ መንግሥቱ ጃንደረቦች ሃማንን ወደ አስቴር ግብዣ በአስቸኳይ ይዘውት ሄዱ።
Currently Selected:
መጽሐፈ አስቴር 6: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997