መጽሐፈ አስቴር 5
5
አስቴር ንጉሡንና ሃማንን ግብዣ እንደ ጠራች
1ጾም በጀመረች በሦስተኛውም ቀን አስቴር ልብሰ መንግሥትዋን ለብሳ በዙፋኑ ክፍል ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ ውስጠኛው የቤተ መንግሥት አደባባይ ገብታ ቆመች፤ ንጉሡም በዚያው ክፍል ውስጥ ከመግቢያው በር ፊት ለፊት በተዘረጋ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ነበር። 2ንጉሡ፥ ንግሥት አስቴር በስተ ውጪ በኩል መቆምዋን በተመለከተ ጊዜ በፊቱ ሞገስን አግኝታ ስለ ነበር የወርቅ በትሩን ዘረጋላት፤ እርስዋም ቀረብ ብላ የወርቁን በትር ጫፍ ነካች። 3ንጉሡም “አስቴር ሆይ፥ ስለምን መጣሽ? ምን እንደምትፈልጊ ንገሪኝ፤ የንጉሠ ነገሥት መንግሥቴን እኩሌታ እንኳ ቢሆን እሰጥሻለሁ” አላት።
4አስቴርም “ንጉሥ ሆይ! መልካም ፈቃድህ ቢሆን ለዛሬ ማታ ባዘጋጀሁት ግብዣ ላይ አንተና ሃማን ብትገኙልኝ እወዳለሁ” አለችው። 5ከዚህም በኋላ ንጉሡ ሃማንን በፍጥነት አስጠርቶ በአስቴር ግብዣ ላይ መገኘት እንዳለባቸው ነገረው፤ ስለዚህም ንጉሡና ሃማን ወደ አስቴር ግብዣ አመሩ። 6የወይን ጠጅ በመጠጣት ላይ ሳሉም ንጉሡ አስቴርን “ማናቸውንም የምትፈልጊውን ነገር ጠይቂኝ፤ ይፈጸምልሻል፤ የመንግሥቴን እኩሌታ እንኳ ብትጠይቂ ልሰጥሽ ዝግጁ ነኝ!” አላት።
7-8አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰችለት፦ “በግርማዊነትዎ ፊት ሞገስ አግኝቼ ግርማዊነትዎ የጠየቅሁትን ነገር ሊፈጽምልኝ ፈቃደኛ ከሆነ ነገ በማዘጋጀው ግብዣ ላይ እርስዎና ሃማን በድጋሚ እንድትገኙልኝ በአክብሮት እለምናለሁ፤ በዚያም ሰዓት የምፈልገውን ነገር እገልጥልዎታለሁ።”
ሃማን መርዶክዮስን ለመግደል መወሰኑ
9ሃማን ከግብዣው ወጥቶ ሲሄድ እጅግ ተደስቶ በልቡም ሐሴት ያደርግ ነበር፤ ነገር ግን ወደ ቤተ መንግሥቱ በሚያስገባው በር አጠገብ መርዶክዮስን ተቀምጦ አየው፤ አልፎም ሲሄድ መርዶክዮስ ከተቀመጠበት ስፍራ እንዳልተነሣለትና ምንም ዐይነት አክብሮት እንዳላሳየው በተመለከተ ጊዜ ሃማን መርዶክዮስን እጅግ ተቈጣው፤ 10ሆኖም እንደምንም ራሱን ተቈጣጥሮ በመታገሥ ወደ ቤቱ ደረሰ፤ ከዚህ በኋላ ወዳጆቹን ወደ ቤቱ ጠርቶ ሚስቱ ዜሬሽም አብራ እንድትገኝ አደረገ። 11ምን ያኽል ሀብታም እንደ ሆነና ምን ያኽል ልጆች እንዳሉት፥ ንጉሡም ሥልጣኑን ከፍ በማድረግና በመሾም የቱን ያኽል እንዳከበረው፥ ከሌሎቹ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ይበልጥ የተከበረ ሰው መሆኑንም በትምክሕት ገለጠላቸው፤ 12ሃማን ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ከዚህም ሁሉ በላይ ንግሥት አስቴር ባዘጋጀችው ግብዣ ላይ ከንጉሡና ከእኔ በቀር ማንንም አልጠራችም፤ ለነገ በምታዘጋጀው ግብዣም ላይ እንደገና ተጠርተናል፤ 13ነገር ግን ያን አይሁዳዊ መርዶክዮስን በቤተ መንግሥቱ መግቢያ በር አጠገብ ተቀምጦ በማየቴ ይህ ሁሉ ክብር ለእኔ ምንም ትርጒም ሊሰጠኝ አልቻለም።”
14ስለዚህ ሚስቱና ወዳጆቹ ሁሉ “ርዝመቱ ኻያ ሁለት ሜትር የሆነ መስቀያ እንጨት አዘጋጅተህ ነገ ጠዋት መርዶክዮስን ለመስቀል የንጉሡን ፈቃድ መጠየቅ ትችላለህ፤ ከዚያም በኋላ ደስ ብሎህ ወደ ግብዣው ትሄዳለህ” ሲሉ ሐሳብ አቀረቡለት። ሃማንም ሐሳቡ መልካም እንደ ሆነ ተቀብሎ የመስቀያውን እንጨት አዘጋጀ።
Currently Selected:
መጽሐፈ አስቴር 5: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997