መጽሐፈ አስቴር 4
4
መርዶክዮስ የአስቴርን ርዳታ መጠየቁ
1መርዶክዮስም ስለ ተደረገው ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ ከዚህም በኋላ ማቅ ለብሶና በራሱ ላይ ዐመድ ነስንሶ ድምፁን ከፍ አድርጎ እየጮኸ በመረረ ሁኔታ በማልቀስ ወደ ከተማይቱ ውስጥ ገባ። 2ማንም ሰው ማቅ ለብሶ ወደ ቤተ መንግሥት መግባት ስለማይፈቀድለት ወደ ቤተ መንግሥት መግቢያ በር ሲደርስ ወደ ውስጥ ዘልቆ መግባት አልቻለም። 3የንጉሡ ዐዋጅ በተላለፈባቸው አገሮች ሁሉ በአይሁድ መካከል ከፍተኛ የለቅሶ ጩኸት ተሰማ፤ እነርሱም መጾምና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማልቀስ ጀመሩ፤ አብዛኞቹም ማቅ ለብሰውና በራሳቸው ላይ ዐመድ ነስንሰው ተቀመጡ።
4የአስቴር ደንገጡሮችና እርስዋን የሚጠብቁ ጃንደረቦች መርዶክዮስ የሚያደርገውን ሁሉ በነገሩአት ጊዜ ጥልቅ ሐዘን ተሰማት፤ ለመርዶክዮስም በማቅ ፈንታ የሚለብሰውን ልብስ ላከችለት፤ እርሱ ግን አልቀበልም አለ። 5ከዚህም በኋላ አስቴር ከቤተ መንግሥቱ ጃንደረቦች መካከል በተለይ እርስዋን እንዲያገለግል ንጉሡ የመደበላትን ሀታክ የተባለውን ጠርታ ወደ መርዶክዮስ ዘንድ ሄዶ ምን እንደ ደረሰበት እንዲጠይቀው ላከችው። 6ሀታክም ወደ ቤተ መንግሥቱ በሚያስገባው በር አጠገብ በሚገኘው የከተማይቱ አደባባይ ወደሚገኘው ወደ መርዶክዮስ ሄደ። 7መርዶክዮስም የደረሰበትን ነገር ሁሉ ዘርዝሮ ነገረው፤ ሃማን አይሁድ ሁሉ የሚገደሉለት ከሆነ ወደ ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤት ምን ያኽል ገንዘብ ለማስገባት ቃል የገባለት መሆኑን ጭምር ገለጠለት። 8የአይሁድን ሕዝብ ለማስፈጀት በሱሳ ከተማ የተላለፈውን የዐዋጅ ቅጂም ለሀታክ ሰጠው፤ ይህንኑ የዐዋጅ ቅጂ ወስዶ ለአስቴር እንዲሰጣትና የሆነውንም ነገር ሁሉ እንዲገልጥላት፥ እንዲሁም ወደ ንጉሡ ዘንድ ገብታ ስለ ሕዝብዋ ምሕረትን እንድትለምን ይነግራት ዘንድ ሀታክን ለመነው። 9ሀታክም ይህን ሁሉ ፈጸመ፤ 10አስቴርም ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ለመርዶክዮስ እንዲነግር ሀታክን መልሳ ላከችው፤ 11“እንደሚታወቀው ሁሉ ወንድም ሆነ ሴት፥ ማንም ሰው ሳይጠራ ወደ ውስጠኛው የቤተ መንግሥቱ አደባባይ ለመግባትና ንጉሡን ለማየት ቢሞክር በሞት ይቀጣል፤ እንግዲህ ሕጉ ይህ ሲሆን፥ ከንጉሡ አማካሪዎች እስከ ሕዝቡ ድረስ ማንም ሰው የሚያውቀው ጉዳይ ነው፤ በሕጉ መሠረት ከሞት ለመዳን የሚችለው ማንም ሰው ወደዚያ በሚገባበት ጊዜ ንጉሡ ፈቅዶ የወርቅ በትሩን ሲዘረጋለት ብቻ ነው፤ እኔ ግን ወደ ንጉሡ ለመግባት ከተጠራሁ እነሆ ሠላሳ ቀኖች አልፈውኛል።”
12መርዶክዮስም የአስቴርን መልእክት ከተቀበለ በኋላ፥ 13ከዚህ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ላከባት፤ “አንቺ በቤተ መንግሥት ለመኖር በመቻልሽ ከሌሎች አይሁድ የተሻለ ዋስትና ያለሽ አይምሰልሽ፤ 14እንደዚህ ባለ ጊዜ ችላ ብለሽ ዝም ብትዪ፥ ለአይሁድ ከሌላ ቦታ ርዳታ መምጣቱ አይቀርም፤ እነርሱም በእርግጥ ይድናሉ፤ አንቺ ግን ትሞቻለሽ፤ የአባትሽም የቤተሰብ ሐረግ ተቋርጦ ይቀራል፤ ነገር ግን አንቺ ንግሥት የሆንሽው በዚህ መከራ ጊዜ እኛን ለመታደግ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?”
15አስቴርም ለመርዶክዮስ እንዲህ ስትል መለሰችለት፦ 16“ሄደህ በሱሳ የሚገኙትን አይሁድ በአንድነት ሰብስብ፤ ጾም ዐውጃችሁም ለእኔ ጸልዩ፤ እስከ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ምንም ዐይነት ምግብ አትብሉ፤ ምንም ዐይነት መጠጥ አትጠጡ፤ እኔና ደንገጡሮቼም በዚሁ ዐይነት እንቈያለን፤ ከዚህም በኋላ በሕግ የተከለከለ ቢሆንም ደፍሬ ወደ ንጉሡ ዘንድ እገባለሁ፤ ይህን በማድረጌ ብሞትም ልሙት።”
17መርዶክዮስም ተነሥቶ ሄደ፤ አስቴር በነገረችውም መሠረት ሁሉን ነገር አደረገ።
Currently Selected:
መጽሐፈ አስቴር 4: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997