መጽሐፈ አስቴር 2:15-23

መጽሐፈ አስቴር 2:15-23 አማ05

በዚህ ዐይነት አስቴር ወደ ንጉሡ ፊት የምትቀርብበት ጊዜ ደረሰ፤ ይህችም አስቴር የአቢኀይል ልጅ፥ እንደ ልጁ አድርጎ ያሳደጋት የመርዶክዮስ የአጐት ልጅ የነበረችውና ባያት ሁሉ ዘንድ ሞገስን ያገኘች ነበረች፤ እርስዋም ወደ ንጉሡ ፊት የመቅረብ ተራዋ በደረሰ ጊዜ የለበሰችው፥ የምርጥ ሴቶች መኖሪያ ቤት ኀላፊ የነበረው ጃንደረባው ሄጋይ እንድትለብስ የመከራትን እንጂ እርስዋ የጠየቀችውን ልብስ አልነበረም። ስለዚህም አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ቴቤት ተብሎ በሚጠራው በዐሥረኛው ወር አስቴር ወደ ቤተ መንግሥቱ ተወሰደች። ንጉሡም ከሌሎቹ ልጃገረዶች ሁሉ አስበልጦ ወደዳት፤ ከሌሎቹም ሁሉ ይበልጥ በፊቱ ሞገስንና መወደድን አገኘች፤ እርሱም መንግሥታዊውን ዘውድ አንሥቶ በራስዋ ላይ ደፋላትና በአስጢን ቦታ አነገሣት። ከዚህም በኋላ ንጉሡ ስለ አስቴር ክብር ታላቅ ግብዣ አዘጋጅቶ ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለሥልጣኖችና አስተዳዳሪዎች ሁሉ ጠራ፤ በንጉሠ ነገሥቱ ግዛት በሚገኙት አገሮች ሁሉ የደስታ በዓል እንዲደረግ ዐወጀ፤ ለጋስነት የተሞላበት ንጉሣዊ ስጦታም አደረገ። ደናግሉ ዳግመኛ በተሰበሰቡ ጊዜ መርዶክዮስ በንጉሡ ቤተ መንግሥት በር ላይ ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር። አስቴርም አይሁዳዊት መሆንዋን ገና አላስታወቀችም ነበር፤ መርዶክዮስም ይህን ለማንም እንዳትናገር በጥብቅ አስጠንቅቆአት ነበር፤ እርስዋም በሕፃንነትዋ ጊዜ በእርሱ ኀላፊነት ሥር ሳለች በሁሉ ነገር ትታዘዘው እንደ ነበር አሁንም በዚህ ነገር ታዘዘችለት። መርዶክዮስ በቤተ መንግሥቱ በር ተቀምጦ በነበረበት ጊዜ ወደ ንጉሡ መኖሪያ ክፍሎች የሚያስገቡትን በሮች ይጠብቁ የነበሩት ቢግታንና ቴሬሽ ተብለው የሚጠሩት ሁለቱ የቤተ መንግሥት ጃንደረቦች በንጉሥ አርጤክስስ ላይ በጠላትነት ተነሣሥተው ሊገድሉት ዐድመው ነበር። መርዶክዮስ ይህን ዐድማ በሰማ ጊዜ ለንግሥት አስቴር ነገራት፤ አስቴርም በመርዶክዮስ ስም ምሥጢሩን ለንጉሡ ነገረች። ምርመራም በተደረገ ጊዜ የቀረበው መረጃ እውነት ሆኖ ተገኘ፤ ስለዚህም ሁለቱ ዐመፀኞች በስቅላት ሞት ተቀጡ፤ ንጉሡም ይህ ሁኔታ በንጉሠ ነገሥቱ የታሪክ መዝገብ ተጽፎ እንዲቀመጥ ትእዛዝ አስተላለፈ።