ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5:8-20

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5:8-20 አማ05

ቀድሞ እናንተ በጨለማ ውስጥ ትኖሩ ነበር፤ አሁን ግን የጌታ ስለ ሆናችሁ ብርሃን ናችሁ ስለዚህ በብርሃን እንደሚኖሩ ሰዎች ተመላለሱ። የደግነት ሁሉ፥ የጽድቅና የእውነት ፍሬ የሚገኘው ከብርሃን ነውና። ስለዚህ ጌታን ደስ የሚያሰኘው ነገር ምን እንደ ሆነ መርምሩ። ወደ ብርሃን አውጥታችሁ አጋልጡት እንጂ ፍሬቢስ ከሆነ ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ። በጨለማ የሚኖሩ ሰዎች በስውር ስለሚያደርጉት ነገር መናገር እንኳ ያሳፍራል። ሁሉ ነገር ወደ ብርሃን ሲወጣ እውነተኛ መልኩ ግልጥ ሆኖ ይታያል። በግልጥ የሚታይ ሁሉ ብርሃን ነው፤ ስለዚህ፦ “አንተ የምታንቀላፋ ንቃ! ከሙታን ተለይተህ ተነሥ! ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሎአል። እንግዲህ እንዴት እንደምትኖሩ በጥንቃቄ አስተውሉ፤ እንደ ጥበበኞች እንጂ እንደ ሞኞች አትኑሩ። ይህ ዘመን ክፉ ስለ ሆነ በማናቸውም አጋጣሚ ጊዜ ተጠቀሙ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። ወደ ጥፋት የሚመራችሁ ስለ ሆነ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይልቅስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ። በመዝሙርና በውዳሴ፥ በመንፈሳዊም ዜማ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በውዳሴና በመዝሙር በሙሉ ልባችሁ ጌታን አመስግኑ፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር እግዚአብሔር አብን ዘወትር አመስግኑ።