ኤፌሶን 5:8-20
ኤፌሶን 5:8-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ ዛሬ ግን በጌታችን ብርሃን ሆናችኋል። እንግዲህስ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ። የብርሃን ፍሬው በጎ ሥራና እውነት፥ ቅንነትም ሁሉ ነውና። እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኘውን መርምሩ። የሥራ ፍሬ ከሌላቸው፥ ሁለንተናቸውም ጨለማ ከሆነ ሰዎች ጋር አትተባበሩ፤ ገሥጹአቸው እንጂ። በስውር የሚሠሩት ሥራ ለመናገር የሚያሳፍር ነውና። ነገር ግን በብርሃን የተገለጠ ሁሉ ይታወቃል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። “የተኛህ ንቃ ከሙታንም ተለይተህ ተነሥ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል” ብሎአልና። እንግዲህ እንደ ዐዋቂዎች እንጂ እንደ አላዋቂዎች ሳይሆን እንዴት እንደምትመላለሱ በጥንቃቄ ዕወቁ። ቀኖች ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት። ስለዚህም ሰነፎች አትሁኑ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አስተውሉ እንጂ። መዳራት ነውና ወይን በመጠጣት አትስከሩ፤ መንፈስ ቅዱስን ተመሉ እንጂ። መዝሙርንና ምስጋናን፥ የተቀደሰ ማሕሌትንም አንብቡ፤ በልባችሁም ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ዘምሩም። ዘወትርም ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና አቅርቡ።
ኤፌሶን 5:8-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ። እንደ ብርሃን ልጆች ኑሩ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ሁሉ ዘንድ ነውና። እንዲሁም ጌታን ደስ የሚያሠኘውን ፈልጉ። ፍሬ ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋራ ምንም ዐይነት ግንኙነት አይኑራችሁ፤ ይልቁን ግለጡት፤ በድብቅ የሚሠሩትን ነገር መናገር ራሱ አሳፋሪ ነውና። ብርሃን የበራበት ነገር ሁሉ ግልጽ ሆኖ ይታያል፤ ምክንያቱም ሁሉን ነገር እንዲታይ የሚያደርገው ብርሃን ነውና፤ ስለዚህም፣ “አንተ የተኛህ ንቃ፤ ከሙታን ተነሣ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሏል። እንግዲህ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። ስለዚህ ሞኞች አትሁኑ፤ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ። በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና። በመዝሙርና በውዳሴ፣ በመንፈሳዊም ዝማሬ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በልባችሁ ለጌታ ተቀኙ፤ አዚሙም። በዚህም እግዚአብሔር አብን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር ሁልጊዜ አመስግኑ።
ኤፌሶን 5:8-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ፥ እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና፤ ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል። እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ።
ኤፌሶን 5:8-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀድሞ እናንተ በጨለማ ውስጥ ትኖሩ ነበር፤ አሁን ግን የጌታ ስለ ሆናችሁ ብርሃን ናችሁ ስለዚህ በብርሃን እንደሚኖሩ ሰዎች ተመላለሱ። የደግነት ሁሉ፥ የጽድቅና የእውነት ፍሬ የሚገኘው ከብርሃን ነውና። ስለዚህ ጌታን ደስ የሚያሰኘው ነገር ምን እንደ ሆነ መርምሩ። ወደ ብርሃን አውጥታችሁ አጋልጡት እንጂ ፍሬቢስ ከሆነ ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ። በጨለማ የሚኖሩ ሰዎች በስውር ስለሚያደርጉት ነገር መናገር እንኳ ያሳፍራል። ሁሉ ነገር ወደ ብርሃን ሲወጣ እውነተኛ መልኩ ግልጥ ሆኖ ይታያል። በግልጥ የሚታይ ሁሉ ብርሃን ነው፤ ስለዚህ፦ “አንተ የምታንቀላፋ ንቃ! ከሙታን ተለይተህ ተነሥ! ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሎአል። እንግዲህ እንዴት እንደምትኖሩ በጥንቃቄ አስተውሉ፤ እንደ ጥበበኞች እንጂ እንደ ሞኞች አትኑሩ። ይህ ዘመን ክፉ ስለ ሆነ በማናቸውም አጋጣሚ ጊዜ ተጠቀሙ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። ወደ ጥፋት የሚመራችሁ ስለ ሆነ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይልቅስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ። በመዝሙርና በውዳሴ፥ በመንፈሳዊም ዜማ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በውዳሴና በመዝሙር በሙሉ ልባችሁ ጌታን አመስግኑ፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር እግዚአብሔር አብን ዘወትር አመስግኑ።
ኤፌሶን 5:8-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ የብርሃን ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና፤ ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን ፈልጉ። ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፤ ይልቁን ግለጡት፤ እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳን ያስነውራል። ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። ስለዚህ “አንተ የምታንቀላፋ ንቃ፤ ከሙታንም ተነሣ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል፤” ተብሏል። እንግዲህ ስለ አኗኗሯችሁ በጥንቃቄ ተጠበቁ፥ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው አይሁን፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ ብክነት እንደ ሆነው በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ።