መጽሐፈ መክብብ 4:1-12

መጽሐፈ መክብብ 4:1-12 አማ05

እንደገናም በዓለም ያለውን የፍርድ መጓደልና ግፍ ተመለከትኩ፤ የተገፉ ጭቊኖች የሚያጽናናቸው አጥተው ያለቅሱ ነበር፤ የፈላጭ ቈራጭነት ሥልጣን በገዢዎቻቸው እጅ ስለ ሆነ የሚረዳቸው አላገኙም። ስለዚህም እኔ “በዚህ ሁኔታ ላይ በሕይወት ካሉት ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱት ይሻላሉ” አልኩ። በተለይም ከነዚህ ከሁለቱ ወገኖች ይልቅ ከቶውኑ ያልተወለዱና በዚህ ዓለም የሚፈጸመውን ግፍና ጭቈና ያላዩ ዕድለኞች ናቸው። ደግሞም ሰዎች የተመኙትን ለማግኘት ተግተው በመሥራት ምን ያኽል እንደሚደክሙ ተመለከትኩ፤ ይህንንም የሚያደርጉት በባልንጀሮቻቸው ላይ በመቅናት መሆኑን ተረዳሁ፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ስለ ሆነ ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው። እጆቹን አጥፎ የሚቀመጥ ሞኝ ሰው ራሱን በራብ ይገድላል። ነፋስን እንደ መጨበጥ ከሚቈጠር ላልተጨበጠ ሐሳብ ብዙ አገኛለሁ ብሎ ከመድከም ይልቅ ከኅሊና ዕረፍት ጋር ጥቂት ለማግኘት መሥራት ይሻላል። በዚህ ዓለም ያለውን ሌላውንም ከንቱ ነገር ተመለከትኩ፤ እነሆ፥ ብቻውን የሚኖር አንድ ሰው አለ፤ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፤ ይሁን እንጂ ዘወትር በሥራ ከመድከም አይቦዝንም፤ ባገኘውም ሀብት በቃኝ ማለትን አላወቀም፤ “እርሱም የምደክመው ለማን ነው? ለራሴስ ደስታን የምነፍገው ለምንድን ነው?” ብሎ ራሱን ይጠይቃል፤ ይህ ሁሉ የባሰ ከንቱና የሥቃይ ሕይወት ነው። የሥራቸው ውጤት መልካም ሊሆን ስለሚችል አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። ከሁለቱ አንዱ ቢወድቅ ሌላው ያነሣዋል፤ ብቻውን የሆነ ሰው ቢወድቅ እንኳ የሚያነሣው ረዳት ስለሌለው ወዮለት። ሁለቱ አብረው ቢተኙ ይሞቃቸዋል፤ ብቻውን የሚተኛ ሰው ግን እንዴት ሊሞቀው ይችላል? አንድ ሰው ብቻውን ሊመልሰው የማይችለውን አደጋ ሁለት ሰዎች ሊቋቋሙት ይችላሉ፤ በሦስት ተሸርቦ የተገመደ ፈትል እንኳ በቀላሉ አይበጠስም።