መጽሐፈ መክብብ 2:17-26

መጽሐፈ መክብብ 2:17-26 አማ05

ከመከራ በቀር ያገኘሁባት ጥቅም ባለመኖሩ ሕይወት በእኔ ዘንድ ትርጒም አልተገኘላትም፤ ይህም ከንቱ ስለ ነበር ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ይቈጠራል። ያለኝን ሀብት ሁሉ ከእኔ በኋላ ለሚተካው ትቼለት ስለምሄድ በዚህ ዓለም የደከምኩበትና ያተረፍኩት ነገር ሁሉ ከንቱ ነው፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ጠቢብ ይሁን ሞኝ ተለይቶ አይታወቅም፤ ይሁን እንጂ እኔ የደከምኩበትንና በጥበቤ ያተረፍኩትን ነገር ሁሉ ወስዶ ባለቤት ይሆናል፤ ይህም ከንቱ ነው። ስለዚህ በዚህ ዓለም የሠራሁትንና የደከምኩበትን ነገር ሁሉ ሳስታውስ ተስፋ አስቈረጠኝ። ባለህ ጥበብ፥ በቀሰምከውም ዕውቀትና ብልኀት የለፋህበትን ሁሉ ምንም ላልደከመበት ሰው ትተህለት ታልፋለህ፤ ይህም ከንቱ ስለ ሆነ ታላቅ መከራ ነው። ታዲያ፥ አስቦና ተጨንቆ በሕይወት ዘመኑ በሚደክምበት ነገር ሁሉ ሰው የሚያተርፈው ቁም ነገር ምንድን ነው? በሕይወቱ ዘመን የሚሠራው ነገር ሁሉ ከሐዘንና ከትካዜ በቀር የሚያተርፍለት ምንም ዐይነት ጥቅም የለም፤ ሌሊት እንኳ አእምሮው ዕረፍት አያገኝም፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ነው። እንግዲህ ለሰው የሚጠቅመው ነገር ቢኖር፥ ደክሞ በመሥራት ያፈራውን ሁሉ በመብላትና በመጠጣት ራሱን ለማስደሰት መቻሉ ነው፤ ይህም ከእግዚአብሔር የተሰጠ መሆኑን ተረድቼአለሁ። ያለ እርሱ ፈቃድማ እየበላና እየጠጣ ተድላ ደስታ ማድረግ የሚችል ማን አለ? እግዚአብሔር ደስ ለሚያሰኘው ሰው ብቻ ጥበብን፥ ዕውቀትንና ደስታን ይሰጠዋል፤ ለኃጢአተኛ ሰው ግን ድካምን ብቻ ያተርፍለታል፤ ስለዚህም እርሱ ያከማቸውን ሀብት ሁሉ ምንም ላልደከመበት እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኝ ለሌላ ሰው ትቶለት እንዲያልፍ ያደርገዋል፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ስለ ሆነ ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው።