መክብብ 2:17-26
መክብብ 2:17-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከፀሐይም በታች የተሠራው ሥራ ሁሉ በእኔ ላይ ክፉ ነውና ሕይወትን ጠላሁ፥ ሁሉም ከንቱ፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። ከእኔ በኋላ ለሚወለድ ሰው እተወዋለሁና ከፀሐይ በታች እኔ የደከምሁበትን ድካም ሁሉ ጠላሁት። ጠቢብ ወይም አላዋቂ እንደሚሆን ከፀሐይ በታችም በደከምሁበትና ጠቢብ በሆንሁበት በድካሜ ሁሉ ይሰለጥን እንደ ሆነ የሚያውቅ ሰው ማን ነው? ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። እኔም ተመልሼ ልቤን ከፀሐይ በታች በደከምሁበት ድካም ሁሉ ተስፋ አስቈረጥሁት። ሰው በጥበብና በዕውቀት በብርታትም ከደከመ በኋላ ለሌላ ላልደከመበት ሰው ዕድሉን ያወርሳልና፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ትልቅም መከራ ነው። ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካምና በልቡ ዐሳብ ሁሉ ለሰው አይሆንለትምና፤ ዘመኑ ሁሉ መከራ፥ ቍጣም፥ ቅሚያም ነው፤ ልቡም በሌሊት አይተኛም፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት በድካሙም ለሰውነቱ መልካም ነገር ከሚያሳያት በቀር በጎ ነገር የለም፤ ይህ ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደ ተሰጠ አየሁ። ያለ እርሱ ፈቃድ የሚበላ ወይም የሚጠጣ ማን ነው? እርሱ በፊቱ ደግ ለሆነ ሰው ጥበብንና ዕውቀትን፥ ደስታንም ይሰጠዋል፤ ለኀጢአተኛ ግን በእግዚአብሔር ፊት ደግ ለሆነ ይሰጥ ዘንድ እንዲሰበስብና እንዲያከማች ጥረትን ይሰጠዋል። ይህ ደግሞ ከንቱ፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
መክብብ 2:17-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ከፀሓይ በታች የሚሠራው ሥራ አሳዛኝ ስለ ሆነብኝ ሕይወትን ጠላሁ፤ ይህም ሁሉ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። ከፀሓይ በታች የደከምሁበትን ነገር ሁሉ ጠላሁት፣ ከኋላዬ ለሚመጣው ሰው የግድ እተውለታለሁና። እርሱ ጠቢብ ወይም ሞኝ ይሆን እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ሆኖም ከፀሓይ በታች ድካሜንና ችሎታዬን ባፈሰስሁበት ሥራ ሁሉ ላይ ባለቤት ይሆንበታል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ስለዚህ ከፀሓይ በታች በደከምሁበት ነገር ሁሉ ላይ ልቤ ተስፋ መቍረጥ ጀመረ፤ ምክንያቱም ሰው ሥራውን በጥበብ፣ በዕውቀትና በብልኀት ሠርቶ፣ ከዚያ ያለውን ሁሉ ለሌላ ላልለፋበት ሰው ይተውለታል። ይህም ደግሞ ከንቱና ትልቅ ጕዳት ነው። ሰው ከፀሓይ በታች በሚደክምበት ጥረትና ልፋት ሁሉ ትርፉ ምንድን ነው? በዘመኑ ሁሉ ሥራው ሥቃይና ሐዘን ነው፤ በሌሊትም እንኳ ቢሆን አእምሮው አያርፍም። ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት፣ በሥራውም ከመርካት ሌላ የሚሻለው ነገር የለውም፤ ይህም ደግሞ ከአምላክ እጅ እንደሚሰጥ አየሁ፤ ከርሱ ዘንድ ካልሆነ ማን መብላትና መደሰት ይችላል? አምላክ፣ ደስ ለሚያሠኘው ሰው ጥበብን፣ ዕውቀትንና ደስታን ይሰጠዋል። ለኀጢአተኛ ግን፣ አምላክን ደስ ለሚያሠኘው ይተውለት ዘንድ፣ ሀብትን የመሰብሰብና የማከናወን ተግባር ይሰጠዋል። ይህም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
መክብብ 2:17-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከፀሐይም በታች የተሠራው ሥራ ሁሉ ከብዶብኛልና ሕይወትን ጠላሁ፥ ሁሉም ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። ከእኔ በኋላ ለሚመጣው ሰው እተወዋለሁና ከፀሐይ በታች የደከምሁበትን ሁሉ ጠላሁት። ጠቢብ ወይም ሰነፍ እንዲሆን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? ከፀሐይ በታች በደከምሁበትና ጠቢብ በሆንሁበት በድካሜ ሁሉ ላይ ጌታ ይሆንበታል፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። እኔም ተመልሼ ልቤን ከፀሐይ በታች በደከምሁበት ድካም ሁሉ ተስፋ አስቈረጥሁት። ሰው በጥበብና በእውቀት በብልሃትም ከደከመ በኋላ ለሌላ ላልደከመበት ሰው ያወርሰዋልና፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ትልቅም መከራ ነው። ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ አሳብ የሰው ጥቅም ምንድር ነው? ዘመኑ ሁሉ ኀዘን፥ ጥረትም ትካዜ ነው፥ ልቡም በሌሊት አይተኛም፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ለሰው ከሚበላና ከሚጠጣ በድካሙም ደስ ከሚለው በቀር የሚሻለው ነገር የለም፥ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደ ተሰጠ አየሁ። ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው? እርሱም ደስ ለሚያሰኘው ሰው ጥበብንና እውቀትን ደስታንም ይሰጠዋል፥ ለኃጢአተኛ ግን እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኘው ሰው ይሰጥ ዘንድ እንዲሰበስብና እንዲያከማች ጥረትን ይሰጠዋል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
መክብብ 2:17-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከመከራ በቀር ያገኘሁባት ጥቅም ባለመኖሩ ሕይወት በእኔ ዘንድ ትርጒም አልተገኘላትም፤ ይህም ከንቱ ስለ ነበር ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ይቈጠራል። ያለኝን ሀብት ሁሉ ከእኔ በኋላ ለሚተካው ትቼለት ስለምሄድ በዚህ ዓለም የደከምኩበትና ያተረፍኩት ነገር ሁሉ ከንቱ ነው፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ጠቢብ ይሁን ሞኝ ተለይቶ አይታወቅም፤ ይሁን እንጂ እኔ የደከምኩበትንና በጥበቤ ያተረፍኩትን ነገር ሁሉ ወስዶ ባለቤት ይሆናል፤ ይህም ከንቱ ነው። ስለዚህ በዚህ ዓለም የሠራሁትንና የደከምኩበትን ነገር ሁሉ ሳስታውስ ተስፋ አስቈረጠኝ። ባለህ ጥበብ፥ በቀሰምከውም ዕውቀትና ብልኀት የለፋህበትን ሁሉ ምንም ላልደከመበት ሰው ትተህለት ታልፋለህ፤ ይህም ከንቱ ስለ ሆነ ታላቅ መከራ ነው። ታዲያ፥ አስቦና ተጨንቆ በሕይወት ዘመኑ በሚደክምበት ነገር ሁሉ ሰው የሚያተርፈው ቁም ነገር ምንድን ነው? በሕይወቱ ዘመን የሚሠራው ነገር ሁሉ ከሐዘንና ከትካዜ በቀር የሚያተርፍለት ምንም ዐይነት ጥቅም የለም፤ ሌሊት እንኳ አእምሮው ዕረፍት አያገኝም፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ነው። እንግዲህ ለሰው የሚጠቅመው ነገር ቢኖር፥ ደክሞ በመሥራት ያፈራውን ሁሉ በመብላትና በመጠጣት ራሱን ለማስደሰት መቻሉ ነው፤ ይህም ከእግዚአብሔር የተሰጠ መሆኑን ተረድቼአለሁ። ያለ እርሱ ፈቃድማ እየበላና እየጠጣ ተድላ ደስታ ማድረግ የሚችል ማን አለ? እግዚአብሔር ደስ ለሚያሰኘው ሰው ብቻ ጥበብን፥ ዕውቀትንና ደስታን ይሰጠዋል፤ ለኃጢአተኛ ሰው ግን ድካምን ብቻ ያተርፍለታል፤ ስለዚህም እርሱ ያከማቸውን ሀብት ሁሉ ምንም ላልደከመበት እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኝ ለሌላ ሰው ትቶለት እንዲያልፍ ያደርገዋል፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ስለ ሆነ ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው።
መክብብ 2:17-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከፀሐይም በታች የተሠራው ሥራ ሁሉ ከብዶብኛልና ሕይወትን ጠላሁ፥ ሁሉም ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። ከእኔ በኋላ ለሚመጣው ሰው እተወዋለሁና ከፀሐይ በታች የደከምሁበትን ሁሉ ጠላሁት። ጠቢብ ወይም አላዋቂ እንደሚሆን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? ከፀሐይ በታች በደከምሁበትና ጠቢብ በሆንሁበት በድካሜ ሁሉ ላይ ይሠለጥንበታል፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። እኔም ከፀሐይ በታች በደከምሁበት ድካም ሁሉ ተመልሼ ልቤን ተስፋ አስቈረጥሁት። ሰው በጥበብና በእውቀት በብልሃትም ከደከመ በኋላ ለሌላ ላልደከመበት ሰው ያወርሰዋልና፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ትልቅም ጉዳት ነው። ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ መጨነቅ የሰው ልጅ ምን ጥቅም ያገኛል? ዘመኑ ሁሉ ስቃይ፥ ጥረትም ትካዜ ነው፥ ልቡም በሌሊት አያርፍም፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ለሰው በመብላትና በመጠጣት፥ እንዲሁም በመጣር ከሚያገኘው ደስታ የሚሻለው ነገር የለም፥ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደተሰጠ አየሁ። ያለ እርሱ ፈቃድ ማን ይበላል፥ ማንስ ተድላን ይቀምሳል? እርሱም ደስ ለሚያሰኘው ሰው ጥበብንና እውቀትን ደስታንም ይሰጠዋል፥ ለኃጢአተኛው ግን እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኘው ሰው ይሰጥ ዘንድ እንዲሰበስብና እንዲያከማች ሥራን ይሰጠዋል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።