የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 27

27
በድንጋይ ላይ የተጻፉት የእግዚአብሔር ሕጎች
1ከዚህም በኋላ ሙሴ ከእስራኤል መሪዎች ጋር ሆኖ ለሕዝቡ እንዲህ አለ፤ “ዛሬ የምሰጣችሁን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ፤ 2የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራችሁ አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በምትገባበት ጊዜ ታላላቅ የሆኑ ጥቂት ድንጋዮችን አቁመህ በኖራ ለስነው፤ #ኢያሱ 8፥30-32። 3የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር በማርና በወተት የበለጸገችውን ምድር እንደሚሰጥህ ቃል በገባልህ መሠረት ምድሪቱን ለመያዝ በተሻገርህ ጊዜ የዚህን ሕግ ቃሎች በድንጋዮቹ ላይ ጻፍ፤ 4ዮርዳኖስን በተሻገርህ ጊዜ እኔ ዛሬ ባዘዝኩህ መሠረት እነዚህን ድንጋዮች በዔባል ተራራ ላይ አቁመህ በኖራ ለስናቸው፤ 5በዚያም የብረት መሣሪያ ካልነካው ድንጋይ መሠዊያ ሥራ፤ 6ለእግዚአብሔር ለአምላክህ የምትሠራው ማናቸውም መሠዊያ ካልተጠረበ ድንጋይ መሆን አለበት፤ በዚያም የሚቃጠል መሥዋዕትህን አቅርብ። #ዘፀ. 20፥25። 7የአንድነት መሥዋዕት አቅርበህ በዚያው እየተደሰትህ በእግዚአብሔር በአምላክህ ፊት ብላ። 8በእነዚያም ድንጋዮች ላይ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ሁሉ በግልጥ እንዲነበቡ አድርገህ ጻፍ።”
9ሙሴም ከሌዋውያን ካህናት ጋር ሆኖ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፥ ከልብ ሆነህ አድምጠኝ፤ እነሆ፥ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነሃል፤ 10ስለዚህም ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዞችና ድንጋጌዎች ሁሉ በመጠበቅ ለእኔ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቃል ታዛዥ ሁን።”
አለመታዘዝ የሚያስከትለው መርገም
11በዚያን ቀን ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ 12“ዮርዳኖስን ከተሻገራችሁ በኋላ ሕዝቡን ለመባረክ በገሪዛን ተራራ ላይ መቆም የሚገባቸው የስምዖን፥ የሌዊ፥ የይሁዳ፥ የይሳኮር፥ የዮሴፍና የብንያም ነገዶች ናቸው። #ዘዳ. 11፥29፤ ኢያሱ 8፥33-35። 13ለእርግማንም በዔባል ተራራ ላይ መቆም የሚገባቸው የሮቤል፥ የጋድ፥ የአሴር፥ የዛብሎን፥ የዳንና የንፍታሌም ነገዶች ናቸው። 14ሌዋውያንም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከዚህ የሚከተለውን ቃላት ይናገሩ፦
15“ ‘እንጨት ጠርቦ፥ ድንጋይ አለዝቦ፥ ብረት አቅልጦ ጣዖት በመሥራት በስውር የሚሰግድለት ማንኛውም ሰው የተረገመ ይሁን! እግዚአብሔር የጣዖት አምልኮን ይጠላል።’ #ዘፀ. 20፥4፤ 34፥17፤ ዘሌ. 19፥4፤26፤ ዘዳ. 4፥15-18፤ 5፥8።
“ሕዝቡም ሁሉ ሲመልሱ ‘አሜን!’ ይበሉ።
16“ ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚያዋርድ የተረገመ ይሁን!’
“ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ” ይበሉ።
# ዘፀ. 20፥12፤ ዘዳ. 5፥16። 17“ ‘የጐረቤቱን ድንበር የሚያፈርስ ሁሉ የተረገመ ይሁን!’
“ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ። #ዘዳ. 19፥14።
18“ ‘ዕውርን ወደተሳሳተ አቅጣጫ የሚመራ ሁሉ የተረገመ ይሁን!’
“ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ። #ዘሌ. 19፥14።
19“ ‘መብት በመግፈፍ መጻተኞችን፥ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆችንና ባሎቻቸው የሞቱባቸው መበለቶችን የሚያንገላታ ሁሉ የተረገመ ይሁን!’
“ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ። #ዘፀ. 22፥21፤ 23፥9፤ ዘሌ. 19፥33-34፤ ዘዳ. 24፥17-18።
20“ ‘የአባቱ ሚስቶች ከሆኑት ከየትኛዋም ጋር ግንኙነት በማድረግ የአባቱን ክብር የሚያዋርድ ሁሉ የተረገመ ይሁን!’
“ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ። #ዘሌ. 18፥8፤ 20፥11፤ ዘዳ. 22፥30።
21“ ‘ከእንስሳ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት የሚያደርግ ማንኛውም ሰው የተረገመ ይሁን!’
“ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ።
22“ ‘ከእኅቱ ወይም በአንድ በኩል ብቻ እኅቱ ከሆነች ሴት ጋር ግንኙነት የሚፈጽም ወንድ ሁሉ የተረገመ ይሁን!’
“ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ።
23“ ‘ከዐማቱ ጋር ግንኙነት የሚፈጽም ወንድ ሁሉ የተረገመ ይሁን!’
“ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ።
24“ ‘በሽምቅ ሰውን መትቶ የሚገድል ሁሉ የተረገመ ይሁን!’
“ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ።
25“ ‘በገንዘብ ተገዝቶ ንጹሑን ሰው የሚገድል ሁሉ የተረገመ ይሁን!’
“ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን!’ ይበሉ።
26“ ‘እነዚህን የእግዚአብሔርን ሕግ ቃላት ሁሉ የማይፈጽም ሁሉ የተረገመ ይሁን።’
“ሕዝቡም ሁሉ ‘አሜን’ ይበሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ