ኦሪት ዘዳግም 28
28
በመታዘዝ የሚገኝ በረከት
(ዘሌ. 26፥3-13፤ ዘዳ. 7፥12-24)
1“ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ብትታዘዝና ዛሬ እኔ የምሰጥህንም ትእዛዞች ሁሉ በታማኝነት ብትጠብቅ፥ በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ 2ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ታዘዝ፤ ከዚህ የሚከተሉት በረከቶች ሁሉ ባለቤት ትሆናለህ፤
3“እግዚአብሔር ከተሞችህንና እርሻዎችህን ይባርካል።
4“እግዚአብሔር ልጆችህን፥ የምድር ፍሬህን፥ የቀንድ ከብትህን፥ የበግንና የፍየል መንጋህን ይባርክልሃል።
5“እግዚአብሔር የእህል ሰብልህንና ቡሃቃህን ይባርካል።
6“እግዚአብሔር መግባትህንና መውጣትህን ይባርክልሃል፤
7“ጠላቶችህ በአንተ ላይ አደጋ በሚጥሉበት ጊዜ እግዚአብሔር እነርሱን ድል ያደርግልሃል፤ በአንድ አቅጣጫ ይመጡብሃል፤ ነገር ግን በሰባት አቅጣጫ ይሸሻሉ።
8“እግዚአብሔር አምላክህ ጐተራህንና የእጅህን ሥራ ሁሉ ይባርክልሃል፤ እንዲሁም በሚሰጥህ ምድር ይባርክሃል።
9“ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ብትታዘዝና ትእዛዞቹንም ሁሉ ብትፈጽም በተስፋ ቃሉ መሠረት ለራሱ የለየህ ወገን ያደርግሃል። 10ከዚያን በኋላ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ የእግዚአብሔር ወገን መሆንክን አይተው ይፈሩሃል። 11እግዚአብሔር ለአንተ ይሰጥህ ዘንድ ለቀድሞ አባቶችህ በማለላቸው ምድር ብዙ ልጆችን፥ ብዙ የቀንድ ከብትና የተትረፈረፈ የእርሻን ሰብል ይሰጥሃል፤ 12በሰማይ ካለው ክምችት ዝናብን በወቅቱ ይልክልሃል፤ የእጅህንም ሥራ ይባርካል፤ ስለዚህም ለብዙ ሕዝቦች ታበድራለህ፤ አንተ ግን ከማንም አትበደርም፤ 13አምላክህ እግዚአብሔር በብዙ ሕዝቦች መካከል እንደ ራስ መሪ ያደርግሃል እንጂ እንደ ጅራት ወደ ኋላ እንድትቀር አያደርግህም፤ ዛሬ እኔ የምሰጥህን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች በታማኝነት ብትፈጽም ምንም ዐይነት ውድቀት ሳይደርስብህ ወደፊት ትገሠግሣለህ እንጂ ወደ ኋላ አትቀርም፤ 14በማናቸውም ሁኔታ ከእነዚህ ትእዛዞች በመውጣት ለባዕዳን አማልክት መስገድና እነርሱን ማገልገል አይገባህም። #ዘዳ. 11፥13፤17።
አለመታዘዝ የሚያስከትለው መርገም
(ዘሌ. 26፥14-46)
15“ነገር ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ባትታዘዝና እኔ ዛሬ የምሰጥህንም ሕጎችና ትእዛዞች በታማኝነት ባትጠብቅ ከዚህ የሚከተለው መርገም ሁሉ ይደርስብሃል፦
16“በከተማም፥ በገጠርም የተረገምክ ትሆናለህ።
17“የእህል ሰብልህና ቡሃቃህ የተረገመ ይሆናል።
18“ልጆችህ፥ የምድርህ ፍሬ፥ የከብት፥ የበግና የፍየል መንጋህ የተረገመ ይሆናል።
19“ስትገባና ስትወጣ የተረገምህ ትሆናለህ።
20“ክፉ ነገር በማድረግ እግዚአብሔርን ስለ ተውክ በምታደርገው ነገር ሁሉ ፈጽመህ እስክትጠፋ ድረስ እርግማንን፥ ሁከትንና ውርደትን ያመጣብሃል። 21ልትወርሳት ከምትገባባት ምድር ጨርሶ እስኪያጠፋህ የማይለቅህን ቀሣፊ በሽታ እግዚአብሔር ያመጣብሃል። #ዘፀ. 22፥19፤ 20፥15። 22እግዚአብሔር በሚያመነምን በሽታ፥ በትኲሳት፥ በቊስል፥ በኀይለኛ ሙቀትና በድርቅ እስክትጠፋም ድረስ ይመታሃል። ሰብልህንም ለማጥፋት ዋግና አረማሞ ይልክብሃል። #ዘሌ. 18፥9፤ 20፥17። 23ሰማይን ከራስህ በላይ እንደ ነሐስ አጠጥሬ ዝናብ እንዳይዘንብ አደርጋለሁ፤ ምድርንም በድርቅ መትቼ እንደ ብረት የጠነከረች አደርጋለሁ። #ዘሌ. 18፥17፤ 20፥14። 24በዝናብ ፈንታ እስክትጠፋ ድረስ እግዚአብሔር በአንተ ላይ በዐውሎ ነፋስ የሚነዳ ትቢያና አሸዋ ይልክብሃል።
25“እግዚአብሔር ለጠላቶችህ በአንተ ላይ ድልን ይሰጣቸዋል፤ በአንድ በኩል ትመጣባቸዋለህ፤ ነገር ግን ከእነርሱ ለማምለጥ በሰባት አቅጣጫ ትሸሻለህ፤ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ በአንተ ላይ የሚደርሰውን ነገር በሚያዩበት ጊዜ በፍርሃት ይሸበራሉ፤ 26በምትሞትበትም ጊዜ ወፎችና የምድረ በዳ አራዊት ሥጋህን ይበሉታል፤ የሚያባርራቸውም አይኖርም፤ #ገላ. 3፥10። 27እግዚአብሔር ልትድን በማትችልበት በግብጻውያን የእባጭ በሽታ፥ በኀይለኛ የጨጓራ በሽታ፥ በቊስልና በሚያሳክክ በሽታ ይመታሃል፤ 28እግዚአብሔር አእምሮ በሚያሳጣ እብደትና ዕውርነት ይመታሃል። 29በእኩለ ቀን እንደ ዕውር ትደናበራለህ፤ የምትሄድበትንም መንገድ ማግኘት አትችልም፤ የምትሠራውም ነገር ሁሉ አይሳካልህም፤ ዘወትር ጭቈናና ምዝበራ ይደርስብሃል፤ የሚረዳህም ሰው አታገኝም።
30“ልጃገረድ ለማግባት ታጫለህ፤ ነገር ግን ሌላ ሰው ይደፍራታል፤ ቤት ትሠራለህ፤ ነገር ግን አትኖርበትም፤ ወይን ትተክላለህ፤ ነገር ግን በፍሬው አትጠቀምበትም። 31ከብትህ በፊትህ፥ ዐይንህ እያየ ይታረዳል፤ ነገር ግን ከሥጋው አትቀምስም፤ አህዮችህ በፊትህ ተስበው ይወሰዳሉ፤ ነገር ግን አይመለሱልህም፤ በጎችህ ለጠላቶችህ ተላልፈው ይሰጣሉ፤ እነርሱን ለማዳን የሚረዳህም የለም፤ 32ዐይንህ እያየ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለባዕዳን ይሰጣሉ፤ የልጆችህን መመለስ በከንቱ በመጠባበቅ ዐይንህ ሲንከራተት ይኖራል፤ ነገር ግን ምንም ለማድረግ አትችልም። 33በከባድ ሁኔታ የደከምክበትን የእህልህን ሰብል የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ አንተ ግን በዘመንህ ሁሉ ግፍና ጭቈና በቀር የሚተርፍህ ነገር የለም። 34የምታያቸው ትርኢቶች ያሳብዱሃል፤ 35እግዚአብሔር ቅልጥምህንና ጭንህን በማይፈወስ ቊስል እንዲሸፈን ያደርጋል፤ ብርቱ ቊስልና እባጭ ከራስ ጠጒርህ እስከ እግር ጥፍርህ ይሸፍንሃል።
36“እግዚአብሔር አንተንና ንጉሥህን ከዚህ በፊት የቀድሞ አባቶችህም ሆኑ አንተ ወዳልነበራችሁበት ባዕድ አገር አፍልሶ ይወስዳችኋል፤ በዚያም ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ባዕዳን አማልክትን ታመልካላችሁ። 37እግዚአብሔር በሚበትንህ አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ በአንተ ላይ የደረሰውን ነገር አይተው ይደነግጣሉ፤ መቀለጃና መዘባበቻም ያደርጉሃል።
38“የእህልህን ሰብል አንበጣ ስለሚበላው ብዙ እህል ዘርተህ ጥቂት መከር ብቻ ትሰበስባለህ፤ 39የወይኑን ሐረግ ትል ስለሚበላው ወይን ተክለህ ትንከባከበዋለህ፤ ነገር ግን የወይን ዘለላ ሰብስበህ አትበላም፤ ወይም ከእርሱ የወይን ጠጅ አትጠጣም፤ 40የወይራ ዛፍ በምድርህ በየስፍራው ይበቅላል፤ ነገር ግን የወይራው ፍሬ ያለ ጊዜው ስለሚረግፍ የወይራ ዘይት አይኖርህም። 41ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትወልዳለህ፤ ነገር ግን የጦር ምርኮኞች ሆነው ስለሚወሰዱ ታጣቸዋለህ፤ 42ዛፎችህንና የእርሻ ሰብልህን ሁሉ ኲብኲባ ይበላዋል።
43“የአንተ ኀይል እየደከመ ሲሄድ፥ በምድርህ የሚኖሩ የመጻተኞች ኀይል ግን ይበረታል። 44መጻተኞች ለአንተ ገንዘብ አበዳሪዎች ይሆናሉ፤ አንተ ግን ለእነርሱ የምታበድራቸው ገንዘብ አይኖርህም፤ በመጨረሻም እነርሱ እንደ ራስ መሪ ይሆናሉ፤ አንተ ግን እንደ ጅራት ወደ ኋላ ትቀራለህ።
45“አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ታዛዥ ሆነህ ስላልተገኘህና እርሱ የሰጠህን ደንቦችና ትእዛዞች ስላልጠበቅህ እነዚህ ሁሉ መቅሠፍቶች ይመጡብሃል፤ ፈጽሞ እስከምትደመሰስ ድረስ ከአንተ አይርቁም፤ 46እነዚህም ሁሉ እግዚአብሔር በአንተና በዘሮችህ ላይ የሰጠውን የቅጣት ፍርድ ለዘለዓለም ሲያስታውሱ የሚኖሩ ምልክቶች ይሆናሉ። 47እግዚአብሔር በብዙ መንገድ ባርኮህ ነበር፤ አንተ ግን ደስታና ሐሴት በተሞላበት ልብ ሆነህ አላገለገልከውም፤ 48ስለዚህም ከእንግዲህ ወዲህ እግዚአብሔር በአንተ ላይ ለሚልካቸው ለጠላቶችህ አገልጋይ ትሆናለህ። በሁሉ ነገር በመቸገርም ትራባለህ፤ ትጠማለህ፤ ትታረዛለህ። ፈጽሞ እስክትጠፋ ድረስ እግዚአብሔር አንተን በጠላቶችህ እንደ ብረት በጠነከረ የአገዛዝ ቀንበር በብርቱ እንድትጨቈን ያደርጋል። 49እግዚአብሔር ቋንቋቸውን የማታውቀውን የሕዝቦች ሠራዊትን ከሩቅ ምድር ያመጣብሃል፤ እነርሱም እንደ ንስር በአንተ ላይ ይወርዱብሃል፤ 50እነርሱ ሽማግሌውን የማያከብሩ፥ ለሕፃንም የማይራሩ ጨካኞች ይሆኑብሃል፤ 51እነርሱ ከብትህንና ሰብልህን ሁሉ ጠራርገው ስለሚበሉት እስክትሞት ድረስ በራብ ትቸገራለህ። እነርሱ አንተ እስክትጠፋ ድረስ ከእህልህ አንዲት ፍሬ፥ ከከብትህ ጥጃ፥ ከበጎችህ መንጋ ጠቦት ከወይንህና ከወይራ ዛፍህ ቅንጣት ፍሬ እንኳ አያስተርፉልህም። 52እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር የሚገኙትን መኖሪያ ከተሞችህን ሁሉ ይከባሉ፤ አንተ የምትተማመንባቸውን ከፍተኞች የሆኑ ቅጽሮች ያሉአቸውን ምሽጎችህን ሁሉ ይደመስሳሉ።
53“ጠላቶችህ ከተሞችህን ከበው በሚያስጨንቁህም ጊዜ፥ የምትበላው አጥተህ ግራ ሲገባህ እግዚአብሔር አምላክህ የሰጠህንና የሆድህ ፍሬዎች የሆኑትን ወንዶችና ሴቶች ልጆችህን ሥጋ ለመብላት ትገደዳለህ፤ 54በመካከላችሁ በመለሳለስና በቅምጥልነት በትውልዱም በመመካት የሚኖረው ሰው እንኳ ለወንድሙ፥ ዐቅፋው ለምትተኛው ሚስቱና ከጥፋት ለተረፉት ልጆቹ ከዚያ ምግብ ለመስጠት ይሰስታል። 55በዚያ ተስፋ በሚያስቈርጠው በከተሞችህ ሁሉ ላይ በሚደረገው በጠላት ከበባ ወቅት ሌላ ምንም የሚበላው ነገር ስለሌለው ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ለማናቸውም አይሰጥም። 56በመለሳለስና በቅምጥልነት በመካከልህ የምትኖር በትውልድዋ የምትመካና ከመለስለስዋ ብዛት እግሮችዋ መሬት ረግጠው የማያውቁ ዐቅፋው ከምትተኛው ባልዋና ከልጆችዋ ትሰስታለች። 57በዚያ ተስፋ በሚያስቈርጠው፥ በከተሞችህ ሁሉ ላይ በሚደረገው የጠላት ከበባ ወቅት ሌላ ምንም የሚበላ ነገር ስለሌላት በምሥጢር ከምትበላቸው ከማሕፀንዋ ከወጡ ልጆችዋና ከእንግዴልጅዋ ለማንም አትሰጥም። #2ነገ. 6፥28-29፤ ሰቆ.ኤ. 4፥10።
58“በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን የእግዚአብሔርን ሕግ ቃላት በጥንቃቄ ባትፈጽሙ፥ አስደናቂና አስፈሪ የሆነውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ስም ባታከብሩ፥ 59እግዚአብሔር በአንተና በልጆችህ ላይ አስፈሪ፥ ለብዙ ጊዜ የሚቈይ መቅሠፍትና ከባድ የማይድን በሽታ ያመጣብሃል። 60በግብጽ ምድር ላይ በወረደ ጊዜ አይተህ ትፈራው የነበረውን ያን አሠቃቂ በሽታ ሁሉ እንደገና በአንተ ላይ ይልካል፤ ከዚያም ደዌ አትፈወስም፤ 61የእግዚአብሔር ሕግ በተጻፉበት በዚህ መጽሐፍ ያልተጠቀሱ በሽታዎችንና መቅሠፍቶችን ሁሉ እስክትጠፋ ድረስ ይልክብሃል። 62ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ታዛዦች ሆናችሁ ስላልተገኛችሁ ብዛታችሁ እንደ ሰማይ ከዋክብት ከነበራችሁት ከእናንተ ጥቂቶቹ ብቻ ይተርፋሉ፤ 63እግዚአብሔር እናንተን ለማበልጸግና ቊጥራችሁንም ለማብዛት እንደ ወደደው ሁሉ እንደገናም እናንተን በማጥፋትና በመደምሰስ ደስ ይለዋል። ከዚህች ከምትወርሱአት ምድር ተነቃቅላችሁ ትጠፋላችሁ።
64“እግዚአብሔር በመላው ዓለም በሕዝቦች መካከል ከአንድ የምድር ዳርቻ እስከ ሌላው ድረስ ይበትንሃል፤ በዚያም አንተም ሆንክ የቀድሞ አባቶችህ ሰግዳችሁላቸው የማታውቁትን ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን ባዕዳን አማልክት ታመልካለህ። 65በእነዚያ ሕዝቦች መካከል ዕረፍትና ለእግርህ ማሳረፊያ ቦታ አይኖርህም፤ እግዚአብሔርም የባባ ልብ፥ በናፍቆት የፈዘዘ ዐይን፥ ተስፋ የቈረጠ ስሜት ይሰጥሃል። 66ሕይወትህ ዘወትር በጭንቀት ላይ ይሆናል፤ የመኖር ዋስትናህም የተረጋገጠ ባለመሆኑ ቀንና ሌሊት በፍርሃት ትዋጣለህ። 67ልብህን በሚሞላው ፍርሀትና በዐይንህ በምታየው አስደንጋጭ ትርኢት ምክንያት፥ ሲነጋ መቼ በመሸልኝ፥ ሲመሽም መቼ በነጋልኝ ትላለህ። 68እግዚአብሔር ‘ዳግመኛ ተመልሰህ ወደዚያ አትሄድም’ ብሎ የተናገረ ቢሆንም እንኳ በመርከብ ተሳፍረህ ወደ ግብጽ እንድትመለስ ያደርጋል፤ በዚያም ራስህን ለጠላቶችህ ባሪያ አድርገህ መሸጥ ትፈልጋለህ፤ ነገር ግን ባሪያ አድርጎ ለመግዛት የሚፈልግህ እንኳ አታገኝም።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 28: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997