የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 19

19
የተለዩ የመማጠኛ ከተማዎች
(ዘኍ. 35፥9-28ኢያሱ 20፥1-9)
1“እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር የሚኖሩትን ሕዝቦች ደምስሶ ከተሞቻቸውንና ቤቶቻቸውንም ወርሰህ በዚያ መኖር በምትጀምሩበት ጊዜ፥ 2-3አምላክህ እግዚአብሔር እንድትኖርባት የሚሰጥህን ምድር ለሦስት ትከፍልና በያንዳንዱ ክፍል አንዳንድ ከተማ የተለየ ታደርጋለህ፤ ነፍሰ ገዳይም ይሸሽባቸው ዘንድ ወደ እነዚያ የሚወስዱትን መንገዶች ታዘጋጃለህ፤ ከዚያ በኋላ አንድ ነፍሰ ገዳይ ሕይወቱን ለማትረፍ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ ሸሽቶ ይሂድ፤ 4አንድ ሰው ቀድሞ ጠላት ያልነበረውን አንድ ሰው የገደለው ሆን ብሎ በማሰብ ሳይሆን በአጋጣሚ አደጋ ምክንያት ሆኖ ከተገኘ አምልጦ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ በመግባት ሕይወቱን ያትርፍ። 5ለምሳሌ፥ ሁለት ሰዎች እንጨት ለመቊረጥ ቢሄዱና አንደኛው እንጨቱን ሲቈርጥ የመጥረቢያው ራስ ከዛቢያው ወልቆ በድንገት ሲወረወር ሌላውን ሰው መትቶ ቢገድል፥ ገዳዩ ከእነዚህ ከሦስት ከተማዎች ወደ አንዲቱ ሄዶ ሕይወቱን ያትርፍ። 6ያለው የመጠለያ ከተማ፥ ርቀቱ ቶሎ የማይደረስበት ቢሆን ግን፥ ደሙን ለመበቀል መብት ያለው የሟቹ ዘመድ አባሮ ይዞ በደል የሌለበትን ያን ሰው በቊጣ ሊገድለው ይችላል፤ በእርግጥም ያ ሰው ጠላቱ ያልሆነውን ሰው የገደለው በአጋጣሚ ነበር። 7ሦስት ከተሞችን እንድትለይ የማዝህ በዚህ ምክንያት ነው።
8“እግዚአብሔር አምላክህ ለቀድሞ አባቶችህ በመሐላ የተስፋ ቃል በገባላቸው መሠረት ግዛትህን ቢያሰፋልህ፥ 9እኔ ዛሬ የማዝህን ትእዛዞች ሁሉ በመፈጸም እግዚአብሔር አምላክህን ብትወድና በመንገዱ ብትሄድ ይህችን ምድር ስለሚሰጥህ ሌሎች ሦስት የመጠለያ ከተሞች ጨምረህ ሥራ። 10ይህንንም የምታደርገው እግዚአብሔር አምላክህ እንድትኖርባት ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ንጹሕ ደም እንዳይፈስስና አንተም የደሙ ተጠያቂ እንዳትሆን ነው።
11“ነገር ግን አንድ ሰው በጠላትነት ተነሣሥቶ በመሸመቅ ሆን ብሎ በጭካኔ ሌላውን ሰው ከገደለ በኋላ ሕይወቱን ለማትረፍ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዲቱ ቢሸሽ፤ 12ገዳዩ የሚኖርበት ከተማ መሪዎች ሰው በመላክ እነርሱም ነፍሰ ገዳዩን አስመጥተው የሟቹን ደም ለመበቀል መብት ላለው የቅርብ ዘመዱ አሳልፈው ይስጡት። 13ለእርሱ ምንም ምሕረት አታድርግለት፤ በሁሉ ነገር መልካም ይሆንልህ ዘንድ ነፍሰ ገዳይን ከእስራኤል አስወግድ።
ቀድሞ የነበረውን ድንበር ማፍረስ እንደማይገባ
14“እግዚአብሔር አምላክህ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ለአንተ በተሰጠው ድርሻና በጐረቤትህ መካከል በቀድሞ ትውልድ የተተከለውን የድንበር ምልክት አታፍርስ።
ስለ ምስክሮች የተሰጠ መመሪያ #ዘዳ. 27፥17
15“የአንድን ሰው ወንጀለኛነት ለማረጋገጥ አንድ ምስክር ብቻ አይበቃም፤ አንድ ሰው ወንጀለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ሁለት ወይም ሦስት ምስክሮች ያስፈልጋሉ። #ዘኍ. 35፥30፤ ዘዳ. 17፥6፤ ማቴ. 18፥16፤ ዮሐ. 19፥31፤ 2ቆሮ. 13፥1፤ 1ጢሞ. 5፥19፤ ዕብ. 10፥28። 16አንድ ክፉ ሰው ሌላውን ሰው በሐሰት ወንጅሎ ቢከሰው፥ 17ሁለቱም ወገኖች እግዚአብሔር በሚመለክበት ቦታ ወደሚገኙት የወቅቱ ካህናትና ዳኞች ወደሆኑት ፊት ይቅረቡ። 18ዳኞቹ ጉዳዩን በጥብቅ ይመረምራሉ፤ ያም ሰው እስራኤላዊ በሆነው ወገኑ ላይ የሐሰት ክስ አቅርቦ ከተገኘ፥ 19ለተከሳሹ ታስቦ የነበረውን ቅጣት እርሱ ይቀበላል፤ ይህን የመሰለ ክፉ ነገር ሁሉ በዚህ ዐይነት ታስወግዳለህ። 20ሰዎች ሁሉ ይህን ስለሚሰሙ ዳግመኛ እንደዚህ ያለ ክፉ ነገር በመካከልህ አያደርጉም፤ 21በእንደዚህ ያለው ክፉ ነገር ላይ ሁሉ ምንም ዐይነት ምሕረት አይኑርህ፤ የቅጣቱም አፈጻጸም ሕይወት ያጠፋ፥ ሕይወቱ እንዲጠፋ፤ ዐይን ያጠፋ፥ ዐይኑ እንዲጠፋ፤ ጥርስ ያወለቀ፥ ጥርሱ እንዲወልቅ፤ እጅ የቈረጠ፥ እጁ እንዲቈረጥ፤ እግርም የሰበረ፥ እግሩ እንዲሰበር በማድረግ ይሁን። #ዘፀ. 21፥23-25፤ ዘሌ. 24፥19-20፤ ማቴ. 5፥38።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ