የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 18

18
የካህናቱና የሌዋውያን ድርሻ
1“ሌዋውያን ካህናት፥ እንዲያውም፥ መላው የሌዊ ነገድ ከቀሩት የእስራኤል ነገዶች ጋር የርስት ድርሻ የላቸውም፤ በዚህ ምትክ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕትና መባ እየተመገቡ ይኖራሉ። 2በወንድሞቻቸው በእስራኤላውያን መካከል ርስት አይኖራቸውም፤ በሰጣቸው ተስፋ መሠረት እግዚአብሔር ርስታቸው ነው። #ዘኍ. 18፥20።
3“የቀንድ ከብት ወይም በግ በሚሠዋበት ጊዜ ካህናቱ ወርቹን፥ አገጩንና፥ ጨጓራውን ይወስዳሉ። 4ከእህልህ፥ ከወይን ጠጅህና ከወይራ ዘይትህ ከተሸለቱ በጎችህም ጠጒር እንኳ ሳይቀር የመጀመሪያውን በኲራት ስጣቸው፤ 5ለዘለዓለም በክህነት ያገለግሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከነገዶቻችሁ መካከል የሌዊን ነገድ መርጦአል።
6“አንድ ሌዋዊ ከሚኖርበት ከማንኛውም የእስራኤል ከተማ እግዚአብሔር ወደሚመርጠው ቦታ ለመምጣት ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖረው፥ 7እዚያ እንደሚያገለግሉት ሌዋውያን ጓደኞቹ በእግዚአብሔር አምላኩ ፊት ያገልግል። 8ከቤተሰብ ንብረት ሽያጭ ገንዘብ የሚቀበል ቢሆንም እንኳ እርሱም ሌሎቹ ካህናት በሚያገኙት መጠን ድርሻውን ይቀበላል።
ከአሕዛብ ልማድ ስለ መጠበቅ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
9“አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በምትገባበት ጊዜ በዚያ የሚኖሩ ሕዝቦች የሚፈጽሙትን አጸያፊ ልማድ ሁሉ አትከተል። 10ማንም ከመካከልህ ወንድ ልጁን፥ ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ አይኑር፤ ወይም አስማተኛ፥ ሟርተኛ፥ ጠንቋይ፥ መተተኛ አይሁን። #ዘሌ. 19፥26፤ ዘፀ. 22፥18። 11ወይም ደግሞ መናፍስትን የሚጠራ ወይም ከመናፍስት ጋር የሚነጋገር፥ ወይም የሙታን መናፍስትን የሚስብ አይኑር። #ዘሌ. 19፥31። 12ይህን የሚያደርግ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላና አጸያፊ ነው፤ አንተ ወደ ፊት በተራመድህ ቊጥር አምላክህ እግዚአብሔር አሕዛብን ከፊትህ ነቃቅሎ የሚያሳድድበት ምክንያት ይህንኑ ዐይነት የረከሰ ሥራ በማድረጋቸው ነው። 13አንተ ግን ለእግዚአብሔር በፍጹም ታማኝ መሆን ይገባሃል።” #ማቴ. 5፥48።
እንደ ሙሴ ያለ ሌላ ነቢይ
14ከዚህ በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፦ “እነዚህ ሀገራቸውን አስለቅቀህ የምትወርስባቸው ሕዝቦች ሟርተኝነትንና ጥንቈላን ይወዳሉ፤ አንተ ግን እግዚአብሔር አምላክህ ይህን እንድታደርግ አይፈቅድም። 15እግዚአብሔር ከወገኖቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ መርጦ ያስነሣላችኋል፤ እርሱ የሚላችሁንም ሁሉ በመስማት ታዛዦች ሁኑ። #ሐ.ሥ. 3፥22፤ 7፥37።
16“በሲና ተራራ ላይ በተሰበሰባችሁበት ቀን እሞታለሁ ብለህ በመፍራት እግዚአብሔር ዳግመኛ እንዳይናገርህና የመገለጡን ሁኔታ የሚያመለክተውን አስፈሪ እሳት እንዳታይ ጠይቀህ ነበር። 17ስለዚህም እግዚአብሔር (ጥያቄው ተገቢ ነው) አለኝ፤ 18እንደ አንተ ያለ ሌላ ነቢይ ከወንድሞቻቸው መካከል አስነሣላቸዋለሁ፤ እርሱ የሚናገረውን ቃል እሰጠዋለሁ፤ እኔም የማዘውን ሁሉ ለሕዝቡ ይነግራል፤ 19በእኔ ስም የሚናገረውን የዚያን ነቢይ ቃል የማይሰማ ሁሉ እቀጣዋለሁ። #ሐ.ሥ. 3፥23። 20ነገር ግን ያላዘዝኩትን ማንኛውንም ነገር በስሜ መናገር የሚደፍር ነቢይ፥ ወይም በሌሎች አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ ይገደል።
21“ ‘አንድ ነቢይ የሚናገረው የትንቢት ቃል ከእግዚአብሔር ያልተሰጠ መሆኑን በምን ለይቼ ዐውቃለሁ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። 22አንድ ነቢይ በእግዚአብሔር ስም ትንቢት ተናግሮ ቃሉ ሳይፈጸም ቢቀር ያ ትንቢት ነቢዩ በግምት የተናገረው ነው እንጂ ከእግዚአብሔር ተሰጥቶት የተናገረው ቃል ስላልሆነ ልትፈራው አይገባም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ